July 24, 2023 – EthiopianReporter.com 

ዜና በጋምቤላ ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት ከ60 በላይ ሰላማዊ ሰዎችና ስምንት የፖሊስ አባላት መገደላቸው…

በጋምቤላ ክልል በተቀሰቀሰ ግጭት ከ60 በላይ ሰላማዊ ሰዎችና ስምንት የፖሊስ አባላት መገደላቸው ተነገረ

ኢዮብ ትኩዬ

ቀን: July 23, 2023

በጋምቤላ ክልል ተቀሰቀሰ በተባለ ግጭት ከ60 በላይ ሰላማዊ ሰዎችና ስምንት የፖሊስ አባላት ሕይወታቸው ማለፉን፣ የክልሉ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመገደላቸው ምክንያት በኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ በአኙዋና በኑዌር ብሔረሰቦች መካከል ግጭቱ መቀስቀሱን፣ በዚህም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

በኢታንግ ልዩ ወረዳና በጋምቤላ ከተማ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ከ60 በላይ ነዋሪዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ከንፁኃን ሰዎች በተጨማሪም ስምንት የፖሊስ አባላት መገደላቸውና የነዋሪዎች ቤቶች መቃጠላቸውን አክለዋል፡፡

እንደ ነዋሪዎች ገለጻ ከሆነ፣ በክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላና በኢታንግ ልዩ ወረዳ ተደረገ በተባለው የተኩስ ልውውጥ፣ ከደቡብ ሱዳን በመነሳት ድንበር ጥሰው ወደ ክልሉ የሚገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎችም ተሳትፈዋል ተብሏል፡፡

በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ንፁኃንና የፖሊስ አባላት መገደላቸውንና መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ ግጭቱን መቆጣጠር መቻሉን፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኦቶው ኦኮት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ግጭቱን ሙሉ ለሙሉ ለማብረድ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በበኩሉ በተቀሰቀሰው ግጭት የመከላከያ ሠራዊት ተሰማርቶ  ፀጥታ እያስከበረ መሆኑን፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

 የፌዴራል ፖሊስ ፀጥታ እያስከበረ መሆኑን ያስታወቀው የሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የብሔርተኝነትና የጎሰኝነት አስተሳሰቦች ክልሉን እየፈኑት መሆኑን አክሏል፡፡

በግጭቱ የሰው ሕይወት ያለፈ በመሆኑ ምክንያት የክልሉ መንግሥት ከሐምሌ 13 ቀን 20015 ዓ.ም. ጀምሮ ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ውጪ የነዋሪዎችና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይኖር፣ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ጭምር የሰዓት እላፊ ገደብ  መጣሉን የክልሉ ካቢኔ አስታውቋል፡፡

ተቀሰቀሰ በተባለው ግጭት ምክንያት በተከሰተው የሰላም መደፍረስ እጃቸው ያለበት አመራሮችም ሆኑ ሌላ አካላት ጉዳይ እንደሚጣራ የክልሉ መንግሥት አክሏል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች፣ ከካምፖች እየወጡ ከታጣቂዎች ጋር በመተባባር በጥቃቱ ሲሳተፉ መመልከታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

የስደተኞቹ ፍላጎት ምን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ስደተኞቹ በኢታንግ ልዩ ወረዳ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ስላላቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡

ከደቡብ ሱዳን የመጡ ከ480 ሺሕ በላይ ስደተኞች በክልሉ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተቀሰቀሰ ግጭት ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ 17 ሰዎች ደግሞ ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ የበርካታ ነዋሪዎች ቤቶች እንደተቃጠለና ለመፈናቀል እንደተገደዱ፣ ግጭቱን ከግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማስቆም መቻሉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡