July 24, 2023 – EthiopianReporter.com

ዜና ከኢዜማ የለቀቁ አባላት ከሌሎች ጋር የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ውይይት መጀመራቸውን አስታወቁ

ከኢዜማ የለቀቁ አባላት ከሌሎች ጋር የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ውይይት መጀመራቸውን አስታወቁ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: July 23, 2023

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከአባልነትና ከአመራርነት የለቀቁ ግለሰቦች የዩኒቨርሲቲ መምህራንን፣ የዳያስፖራ አባላትንና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችን በማካተት በቅርቡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ንቅናቄ ለመመሥረት የሚያስችላቸውን የመጀመርያ ውይይት መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡

የጀመሩትን ውይይት አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የትግል ጉዞ መድከም፣ መውደቅና ውጤት አልባነት የአገዛዞች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመፍጠር ቀናዒነት ማጣትና የአፈና ጡንቻ መፈርጠም ዋነኛ ምክንያቶች ቢሆኑም፣ ያልዳበረው የውስጠ ፓርቲ የፖለቲካ ባህልና አሠራርም ሌላኛው ጎልቶ ሊጠቀስ የሚችል ችግር ነው ብለዋል፡፡

የአገር ሰላምና ህልውናን ለማቅናትና የሕዝቧን አብሮነት ለማስጠበቅ ነባር ፖለቲካዊ ባህል በመገምገም፣ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለመትከል በጋራ የሚቆምበት ወሳኝ ጊዜ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ ከኢዜማ ድርጅታዊ መዋቅር የለቀቁ አመራሮችና አባላት ከሌሎች ስብስቦች ግለሰቦች ጋር በመሆን ለአዲስ ፖለቲካዊ ባህል ግንባታ ጠቀሜታ አላቸው ባሏቸውና ለቀጣዩ ፖለቲካዊ የትግል ጉዞ በሚያግዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግምገማ፣ ውይይትና ምክክር መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የመደራጀት ፍላጎት ካላቸው ስብስቦችና ግለሰቦች ጋር በተመረጡ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች በማዘጋጀት ዘመኑ በሚፈቅደው ሁኔታ   ውይይት እየተካሄደበት መሆኑን መግለጫው አትቷል፡፡ ውይይቱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል፣ ልማድ፣ ዕሳቤ፣ የአሠራር ዘይቤ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነትን የሚጠግን፣ ለችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችል ‹‹ችግር ፈቺ›› የሐሳብ ግብዓትና ለወቅቱ የሚመጥን ሰላማዊ የትግል አማራጭ ለመወሰን የሚያስችል አቅም ያለው ውይይት እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የስብስቡ አስተባባሪ ከሆኑት መካከል የቀድሞው የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ የሽዋስ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከኢዜማ የወጡና በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩ በርካታ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሐሳብ አንድነት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ውይይት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተካተውበታል ብለዋል፡፡

የተጀመረው ውይይት በዋነኝነት በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበረውን የፖለቲካ ሒደት መገምገም፣ ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ታሪክ መቃኘትና መገምገም፣ በተለይም ከተፈጠሩ ስህተቶች በመማር የብሔርና የዜግነት ፖለቲካ ላይ ውይይት በማድረግ አስታራቂ ዕሳቤዎችን በመፍጠር ዋነኛ አጀንዳዎች ምን መሆን አለባቸው የሚሉት ይዳሰሳሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹በእኛ እምነት በብሔረሰብ፣ በሃይማኖትና በመሳሰሉ ነገሮች የሚደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ ስብስቦች ብዙ ርቀት ይወስዳሉ ብለን ስለማናስብ፣ መፈታት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስተካከል የሚችሉ አጀንዳዎች ተለይተው የመጡበትን ሁኔታ በመገምገም እንዴት መፈታት አለባቸው በሚለው ላይ ጥሩ ውይይት በማድረግ ረዥም ርቀት እንዲያስኬድ ታስቦ የተቀየሰ ነው፤›› በማለት አቶ የሽዋስ ገልጸዋል፡፡     

የስብስቡ አስተባባሪ የሆኑትና ሌላው የቀድሞ የኢዜማ አመራር አቶ ኑሪ ሙዲሲር ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም ፓርቲ ለመመሥረት ፍላጎት የነበራቸው ዜጎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ዳያስፖራዎችን በማካተት የተዋቀረ ስብስብ ነው፡፡

ከዚህ በፊት እንደታው የተለያዩ ግለሰቦች ሲሰባሰቡ በየጊዜው እየተሰነጠቀና እየተሰነጠረ እንዳይኬድ፣ የሚነሱ ችግሮችን ከአሁኑ በመፍታት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት የሚል እምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ ኢዜማን ስንመሠርት እዚህ ደረጃ እንደርሳለን ብለን አስበን አናውቅም ነበር፡፡ በመሆኑም ሒደቱ ከጅምሩ ካልተስተካከለለት የሚወርደውን ውኃ መገደብ እንደማያቆመው ሁሉ፣ ይህ ስብስብም አሠራሩን ከጅምሩ ግልጽና አሳታፊ በማድረግ በግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ተቋም ላለመመሥረት ጥረት ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡