
ከ 5 ሰአት በፊት
ሩስያ ሰኞ ንጋት ዩክሬን ሞስኮ ከተማ ላይ በፈጸመችው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት በሁለት ሕንጻዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገለጸች።
የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ሁለቱ ድሮኖች ተመትተው እንዲወድቁ መደረጋቸውን እና በድሮን ጥቃቱ ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ አስታውቋል።
በሩስያ መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው ታስ የተባለው የዜና ወኪል ሁለተኛው ድሮን መከላከያ ሚኒስቴር ቢሮ አቅራቢያ ተመትቶ መውደቁን ዘግቧል።
ከመከላከያ ሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የድሮን ስብርባሪዎች መገኘታቸው ተዘግቧል።
የዩክሬን አመራሮች የደሮን ጥቃቱ ስለመፈጸሙ ያሉት ነገር የለም። ከዚህ ቀደምም በሩስያ ውስጥ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች የዩክሬን ባለስልጣናት ማረጋገጫ አይሰጡም።
የሞስኮ ከተማ ከንቲባ ሰርጌይ ሶብያኒን የድሮን ጥቃቶቹ የሰዎች መኖሪያ ያልሆኑ ሕንጻዎችን ዒላማ ማድረጋቸውን እና በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ንጋት 10 ሰዓት ላይ በደረሰው ጥቃት ሕንጻዎቹ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተናግረዋል።
“የኪዬቭ አምባገነን መንግሥት ሁለት ድሮኖችን በመጠቀም በሞስኮ ግዛት ላይ ለማድረስ ያሰበው የሽብር ጥቃት እንዲቆም ተደርጓል” ብሏል የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ።
- ትዊተር አርማውን ከምናውቃት ወፍ ወደ ‘ኤክስ’ ምልክት ሊቀይር መሆኑን ኢላን መስክ ገለጠከ 5 ሰአት በፊት
- የትግራይ ቤተ ክህነት የስድስት ኤጲስ ቆጶሳትን ሹመት አከናወነ23 ሀምሌ 2023
- ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ‘ጃ’ በዓለም አቀፉ ምናብ23 ሀምሌ 2023
የድሮን ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የትራፊክ እንቅስቃሴ ቆሞ ነበር። በአካባቢው በርካታ የድንገተኛ ጊዜ ሠራተኞችም ታይተው ነበር።
ሞስኮ በኪዬቭ የድሮን ጥቃት እየደረሰብኝ ነው ስትል ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሳምንታት በፊት ዩክሬን የድሮን ጥቃቶችን ሞስኮ ላይ መክፈቷን ሩስያ ገልጽ ነበር።
ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ደግሞ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሕይወትን ለማጥፋት ዩክሬን ክሬምሊን ላይ የድሮን ጥቃት ሙከራ አድርጋለች ተብሎ ነበር።
=ዩክሬን በሞስኮ ላይ ያነጣጠሩ የድሮን ጥቃቶችን ፈጽማላች የተባለው ሩስያ በዩክሬኗ የወደብ ከተማ ኦዴሳ ላይ አዲስ የሚሳኤል ጥቃቶችን መሰንዘር ከጀመረች በኋላ ነው።
ኦዴሳ ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ታሪካዊ ቀርሶች መውደማቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የባህል ኤጀንሲ የሆነው ዩኔስኮ ጥቃቱን አጥብቄ አወግዛለሁ ብሏል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ደግሞ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።
ዜሌንስኪ ለዚህ ጥቃት ሩስያ ዋጋውን ትከፍላለች ካሉ በኋላ፤ “የእነዚህ ሚሳኤሎች ዒላማ ከተማዎች፣ መንደሮች እና ሰዎች ብቻ አይደሉም። ዒላማቸው ሰብዓዊነት እና የጠቅላላው የአውሮፓ ባሕል መሠረት ነው” ብለዋል።