ኢላን መስክ

ከ 5 ሰአት በፊት

የትዊተር ባለቤት ኢላን መስክ የትዊተር ‘ሎጎ’ ከተለመደው የወፍ ምልክት ወደ ‘ኤክስ’ [X] ሊቀይር መሆኑን ገልጧል።

ነገር ግን ኢላን መስክ ይህን አደርጋለሁ ብሎ ከመፈፀም ይቦዝናል፤ አሊያም ቁም ነገር ሳይሆን ዋዛ ሆኖ ይገኛል።

የቢዝነስ አርማውን ወደ ኤክስ ኮርፕ የቀየረው መስክ “እንደውም ይህን ሊሆን የሚገባው ቀድሞ ነበር” ብሏል።

ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ቢሊየነሩ ልክ እንደ ቻይናው ዊቻት ኤክስ የተባለ “ሁሉን ያካተተ” መተግበሪያ የመሥራት ሐሳብ አለው።

የትዊተር አርማ የሆነችው ወፍ እንደምትቀየር እሑድ ዕለት ያሳወቀው መስክ “በቃ ሁላችንም የትዊተር አርማን ቻው የምንልበት ጊዜ ተቃርቧል። ቀስ በቀስ ደግሞ ሁሉንም ወፎች” ብሏል።

የዛኑ ዕለት አዲስ ጊዜያዊ አርማ ይፋ እንደሚደረግም ያሳወቀው መስክ የእንግሊዝኛ ኤክስ ፊደል ምልክት ያለበት አርማ ለጥፏል።

የትዊተር ሥራ አስፈፃሚ ሊንዳ ያካሪኖ በትዊተር ገፃቸው አርማ መቀየሩ አስደሳችና አዲስ ጅማሮ ነው ብላለች።

በእስያ ሃገራት ለምሳሌ በሕንድ ፔይቲኤም፤ በኢንዶኔዥያ ደግሞ ጎጄክ የሚባሉ መተግበሪያዎች ሁሉን አቀፍና በርካቶች የሚጠቀሙባቸው ናቸው።

መተግበሪያዎች ተጠቃሚዎች ለሚፈልጉት አገልግሎት ክፍያ እንዲፈፅሙም ያስችላሉ።

በመልዕክት መላላኪያነት የጀመረው የቻይናው ዊቻት አሁን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች የሚጠቁመትና በርካታ አገለግሎት የሚሰጥ መተግበሪያ ሆኗል።

ባለፈው ዓመት ቻይና ውስጥ ብቻ 1.29 ቢሊዮን ሰዎች ይህን መተግበሪያ እንደሚጠቀሙ ተነግሯል።

ጥቅምት 2022 ትዊተርን የገዛው ኢላን መስክ የንግድ ስሙን ወደ ኤክስ ኮርፕ [X Corp] ቀይሯል።

የትዊተር ድረ-ገፅ እንደሚለው ሰማያዊ ቀለም ያላት ወፍ “እጅግ ልዩ የሆነች ንብረታችን ናት። ለዚህ ነው የምንጠብቃት።”

ኩባንያው ባለፈው ሚያዚያ ለአጭር ጊዜ አርማውን ዶጅኮይ በተሰኘው ክሪፕቶከረንሲ አርማ ቀይሮ እንደነበር ይታወሳል።

ነገር ግን ኢላን መስክ በኋላ የዶጅኮይን ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል በሚል ከክሪፕቶከረንሲ ኢንቨስተሮች ወቀሳ ደርሶበት ነበር።

መስክ፤ በያዝነው ወር መባቻ የትዊተር ተጠቃሚዎች በቀን ማየት የሚችሉት ‘ትዊት’ ይገደባል ማለቱን ተከትሎ ተጠቃሚዎች አመፅ ቀስቅሰው እንደነበር አይዘነጋም።

ይህን ተከትሎ የሜታ ባለቤት የሆነው ማርክ ዛከርበርግ ትሬድስ የተሰኘ ከትዊተር የሚመሳሰል መተግበሪያ ሰርቶ ለገበያ በማቅረብ በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ማገበሱን ገልጧል።

ከመገናኛ ብዙሃን አፍ የማይጠፋው የመስክ ትዊተር ባለፈው ማክሰኞ ክስ ተመስርቶበታል።

የቀድሞ ሠራተኞች ሥራ ሲለቁ ሊከፈላቸው የሚገባ 500 ሚሊዮን ዶላር ኩባንያ ሊከፍል ይገባል ይላል የክስ መዝገቡ።

ኢላን መስክ ትዊተር ከገዛው በኋላ ኩባንያው ከግማሽ በላይ ሠራተኞችን አባሯል።