
ከ 20 ደቂቃዎች በፊት
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለዓመታት ታስረዋል የተባሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አመራሮች እንዲለቀቁ ጠየቀ።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው መግለጫ ሰባቱ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች በፖለቲካ ተሳትፏቸው ብቻ ለሦስት ዓመታት ያህል በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን ማሻሻል እንዳለበት ማሳያ ነው ብሏል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦሮሚያ ፖሊስ አብዲ ረጋሳ፣ ዳዊት አበደታ፣ ለሚ ቤኛ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ኬነሳ አያና እና ገዳ ኦልጅራ የተባሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፍርድ ውጭ ላለፉት ዓመታት ይዞ እንደሚገኝ ገልጿል።
“የፖሊስ አዛዦች የኦሮሞ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ለረዥም ጊዜ እና ጭካኔ በተሞላበት የእስር ሁኔታ ውስጥ በመያዝ በኢትዮጵያ ፍትሕ ሥርዓት ላይ እያፌዙ ነው” ብለዋል የአፍሪካ የሂዩማን ራይትስ ዎች ምክትል ዳይሬክተር ላቲሻ ባደር።
ፍርድ ቤት ግለሰቦቹ ከእስር እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ የሰጠው ትዕዛዝ ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱን እና ባለሥልጣናት የፖለቲካ ኃላፊዎቹን አስሮ ለማቆየት ምንም አይነት ሕጋዊ ምክንያት እንደሌላቸው ሂዩማን ራይትስ ዋች ገልጿል።
የመብት ተማጋቹ ሪፖርቱን ያጠናቀረው የታሰሪ ሰዎች ቤተሰቦችን እና ጠበቆችን፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችን በማነጋገር እና የፍርድ ቤት እንዲሁም የሕምክና ሰነዶችን ከመረመረ በኋላ ነው።
በእስር ላይ ከሚገኙት አመራሮች መካከል አንዱ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አብዲ ረጋሳ ይገኙበታል።
- ጠጥተው ሲያሸከረክሩ የተገኙት የኒው ዚላንድ ፍትሕ ሚንስትር ከሥራ ተሰናበቱከ 2 ሰአት በፊት
- ኢሰመኮ በጋምቤላ ያለው የፀጥታ ችግር የመንግሥትን ተጨማሪ ትኩረት የሚሻ ነው አለከ 2 ሰአት በፊት
- የህዋ ሕክምና ምርጥ ተማሪ ተብሎ የተሸለመው ኢትዮጵያዊው የቀድሞ አየር ኃይል አባልከ 5 ሰአት በፊት
አብዲ ረገሳ ጥር 2012 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ቡራዩ ውስጥ የፖሊስ አባል ገድዋል በሚል ተጠርጥረው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው በኋላ ለወራት ያሉበት ሳይታወቅ የኦሮሚያ ፖሊስ ቢያንስ በተለያዩ ስምንት ቦታዎች እያዘዋወር አስሯቸው ቆይቷል።
ፖሊስ ለሚ ቤኛ፣ ዳዊት አብደታ፣ ኬነሳ አያና እና ሚካኤል ቦረን ደግሞ ሐምሌ 2012 ዓ.ም. የአርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከበርካታ ፖለቲከኞች ጋር ነበር በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
ልክ እንደ አብዲ ረጋሳ ሁሉ ኦሮሚያ ፖሊስ ሐምሌ 2012 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋላቸውን ግለሰቦች ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ በተለያዩ ቦታዎች እያዘዋወር አስሮ ማቆየቱን ለተሟጋች ቡድኑ ቃላቸውን የሰጡ የቤተሰብ አባላት ተናግረዋል።
“የት እንደነበሩ ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ አናውቅም ነበር። . . . በሕይወት ስለመኖራቸው ሁሉ ተስፋ ቆርጠን ነበር. . . በየፖሊስ ጣቢያዎቹ እየሄድን የት እንደሚገኙ እና በሕይወት እንዳሉ እንጠይቅ ነበር። ፖሊስ ግን የት እንዳሉ እንደማያውቅ ይነግረን ነበር” ብለዋል አንድ የታሳሪ ቤተሰብ አባል።
ኦሮሚያ ፖሊስ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ላይ እነዚህን ሰባት እስረኞች ከቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ አውጥቶ አድራሻው ወዳልተጠቀሰ ስፍራ አዘዋውሯቸዋል። የቤተሰብ አባላት እንደሚሉት ከሆነ ፖሊስ እስረኞቹን ከቡራዩ ወደ ሌላ ስፍራ ያዘዋወረው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እስረኞቹን ሊጎበኝ አንድ ቀን ሲቀረው ነበር።

ሰባቱ እስረኞች ከሳምንት በኋላ ዱከም ከተማ ታስረው እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ፖሊስ እስረኞቹን ከቡራዩ ወደ ዱከም ለምን እንዳዘዋወር የሰጠው ማብራሪያ አለመኖሩን የጠበቃ ቡድን አባል ለሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች በመንግሥት ይዞታ ስር የሚገኝ ሰውን አድራሻ ይፋ አለማድረግ፣ ሰዎችን በኃይል ከመሰወር ጋር የሚመጣጠን የዓለም አቀፍ ወንጀል ነው ብሏል።
ግንቦት 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ከሕግ ውጪ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጾ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር።
እነዚህ ሰባት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ከእስር እንዲለቀቁ የፌደራል እና የክልል ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጂ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር አውሏቸው ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ሕግም በሚካኤል ቦረና፣ ኬነሳ አያና እና ገዳ ገቢሳ ላይ ከፍቶት የነበረውን የክስ መዝገብ በማስረጃ እጦት ዘግቶታል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት፣ ጠበቆች እና የፖለቲካ ሰዎች ከሕግ ውጪ በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ የሚሏቸው ሰባት ሰዎች ነጻ ለማውጣት ሁሉንም አማራጭ ተጠቅመዋል።
“በእነርሱ ጉዳይ፤ ምንም አይነት ሕጋዊ አካሄድ የለም። ግራ የሚያጋባን ነገር፤ ግልጽ ያልሆነልን ነገር . . . የፍርድ ቤት ቀጠሮ የለም። አልተፈረደባቸውም፤ መፈታት ነበረባቸው። ግን አሁን በእስር ሆነው ዓመታት እያለፉ ነው” ብለዋል አንድ የቤተሰብ አባል።
የተጠቀሱትን እስረኞች በተመለከተ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ አስካሁን ያሉት ነገር የለም።