ኤም-ፔሳ ገንዘብ መላላኪያ

ከ 13 ደቂቃዎች በፊት

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ ኤም-ፔሳ የተሰኘው የሞባይል ገንዘብ መላላኪያ አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀምር ገለጸ።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እናት ድርጅት የሆነው ቮዳኮም ግሩፕ ሊሚትድ የኤም-ፔሳ አገልግሎት መስከረም 2016 ዓ.ም. አጋማሽ እንደሚጀመር ገልጧል።

ቮዳኮም ግሩፕ የ2023 አንደኛ ሩብ ዓመት በዳሰሰበት መግለጫው በሁለተኛው ሩብ ዓመት ኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ይጀምራል።

እአአ ጥቅምት 2022 ሥራ የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከ2.7 ሚሊዮን ባለይ ደንበኞች ማካበቱን መግለጫው ያትታል።

ግዙፉ የቴሌኮም ድርጅት በፈረንጆቹ 2027 ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ትርፍ ማግኘት እንደሚጀምር ይገምታል።

ባለፈው ግንቦት በሳፋሪኮም የሚመራው ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ መላላኪያ ሥራ ለመጀመር ፈቃድ ያገኘ የመጀመሪያው የውጭ ድርጅት ሆኗል።

ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኤም-ፔሳ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ፈቃድ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው።

በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ውስጥ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን የግብይት ሥርዓት በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች መተካትን እና መስፋፋትን በጥብቅ እንደሚደግፍ ብሔራዊ ባንኩ በወቅቱ መግለጡ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ክፍት ባደረገቻቸው የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቶች ውስጥ የሞባይል ባንክ አገልግሎት እና የባንክ ካርድ አገልግሎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በፍጥነት መስፋፋቱም ተመልክቷል።

ኤም-ፔሳ የሚሠራው እንዴት ነው?

ኤም-ፔሳ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ነው።

መሥራቹ የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ሲሆን፤ አሁን ላይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተተገበረ ይገኛል።

ኤም-ፔሳ ሰርዓት ከሲም ካርድ ጋር ከተያያዘ በኋላ ተጠቃሚዎች በስልካቸው አማካይነት ገንዘብ ማስቀመጥ፣ ገንዘብ መቀበል፣ ክፍያ መፈጸም፣ ከባንክ እና ወደ ባንክ ገንዘብን ማዘዋወር፣ ገንዘብ ለሌላ ኤም-ፔሳ ተጠቃሚ መላክ እና ሌላም የገንዘብ ልውውጥ ማካሄድ ይቻላሉ።

እአአ በ2007 በሳፋሪኮም እና ቮዳፎን የተጀመረው ኤም-ፔሳ፤ ኬንያ ውስጥ የሚተዳደረው በኬንያ ብሔራዊ ባንክ ነው።

ኤም-ፔሳ የሚለው መጠሪያ ውስጥ ኤም ሞባይልን ሲወክል፣ ፔሳ ደግሞ በስዋሂሊ ገንዘብ ማለት ነው።

የገንዘብ ልውውጥን የሚያሳልጡ የሳፋሪኮም ተወካዮች በተለያዩ መደብሮች ይገኛሉ። ለእነዚህ ተወካዮች ጥሬ ገንዘብ በመስጠት ወደ ኤም-ፔሳ ገንዘቡን እንዲያዘዋውሩ ማድረግ ይቻላል።

በኤም-ፔሳ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ያለ ገንዘብን በጥሬ ገንዘብ ከተወካዮቹ የመውሰድ አማራጭም አለ።

በተለይ ኬንያ ውስጥ ከጉሊት አንስቶ እስከ ቅንጡ ሆቴሎች ድረስ ክፍያ የሚፈጸመው በኤም-ፔሳ ነው።

50 በመቶ የሚሆነው የኬንያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) በዚሁ ሥርዓት በኩል ይንቀሳቀሳል።

ኢትዮ ቴሌኮም ገንዘብ ለመቀበል፣ ለመላክ፣ የግብይት እና የአገልግሎትን ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም ከውጭ አገራት ገንዘብ መቀበል የሚያስችለውን ቴሌ ብር ከሁለት ዓመት በፊት መጀመሩ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎቶች በባንክ እና በመሰል ተቋማት ብቻ እየተሰጠ የነበረው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ላይ ማሻሻያ በመደረጉ ነው ኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ መሳተፍ የጀመረው።

ኤም-ፔሳ

የኬንያው ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው መስከረም 26/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ለ125 ዓመታት በላይ በመንግሥት የልማት ድርጅት በብቸኝነት ተይዞ የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ክፍት በማድረግ የቴሌኮም ፈቃድ የሰጠችው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመሰማራት በተደረገው ዓለም አቀፍ ጨረታ በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በ850 ሚሊዮን ዶላር ማሸነፉ ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተሰኘው ይህ ጥምረት፣ በዘርፉ አሉ የሚባሉ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችን እና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ሲሆን እነዚህም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ እና ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እንዲሁም ሲዲሲ ግሩፕ የተካተቱበት ነው።