July 24, 2023 – EthiopianReporter.com 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም እንዲፈጠር ላበረከቱት አስተዋጽኦ በሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ዕውቅና ሲሰጣቸው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ተገኝተው ነበር

የኢትዮ ኤርትራ ጉርብትና ከየት ወዴት

ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

July 23, 2023

የዛሬ አምስት ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኤርትራ መዲና አስመራ መርገጣቸው እንደ ትልቅ ተዓምር የተቆጠረ አጋጣሚ ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) በአስመራ ቤተ መንግሥት የክብር እንግዳ በሆኑበት በልዩ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ በአንዲት ሴት ድምፃዊ ሲንቆረቆር የተደመጠው የኪሮስ ዓለማየሁ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃ ደግሞ፣ የሁለቱን አገሮች የብዙ ዓመታት ታሪክ በወለብታ የሚያስታውሱ ግጥሞች ነበሩት፡፡

አለሁዬ ዝብልዬ

የለሁ ናይ ጣዕሙን፣

መቀናይ ፅቡቅዩ

ወላ ነሃደ ሰሞን፣

ሁሉ ንምእራይ

ምቅናይ ምቅናይ፣

ከአስመራ ቤተ መንግሥት በሴት ድምፃዊት የተንቆረቆረው የኪሮስ ዓለማየሁ ‹‹ምቅናይ›› ጊዜ ደጉ ብዙ ያሳየናል የሚል ጥቅል ፍቺ ነበረው፡፡ ‹‹መቆየትና መሰንበት ደጉ ብዙ ነገር ሲቀየር በዓይን ያስመለክተናል›› የሚል ትርጓሜ የያዘው ዘፈኑ፣ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ሲፈላለጉ የቆዩት ኤርትራና ኢትዮጵያ ጊዜ አልፎ ሲታረቁ በታየበት ቀን መዘፈኑ ትልቅ ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ነበር፡፡

የዓብይ (ዶ/ር) አስመራን መርገጥ፣ የምቅናይ በአስመራ ቤተ መንግሥት መዘፈን ልክ እንደ ልዩ ተአምር መነጋገሪያ ሆኖ ሰነበተ፡፡ ብዙም ሳይዘገይ ደግሞ የኤርትራ ፕሬዚዲንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ መምጣት ሌላ ተአምር ፈጠረ፡፡ ኢሳያስ አዲስ አበባ የገቡ ቀን የተፈጠረውን የሕዝብ ደስታና ስሜት በቃላት መግለጽ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡

በዚያው ሰሞን ኢሳያስና ዓብይ (ዶ/ር) በሚሊኒየም አዳራሽ የሚታደሙበት ልዩ የአቀባበል ምሽት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የዚያን ዕለት ምሽት ግን ሩሲያ ያስተናገደችው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ግጥሚያ በፈረንሣይና በክሮሺያ መካከል ሊካሄድ መርሐ ግብር ወጥቶ ነበር፡፡

እግር ኳስ በኢትዮጵያ እጅግ ይወደዳል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያና የኤርትራ መታረቅን የሚያክል ክብደት ያለው ጉዳይ በዚያን ሰሞን አልነበረም፡፡ በአንዳንድ መዝናኛ ሥፍራዎች ‹‹ኳስ አጥፉልን›› የሚል ጥያቄ መቅረቡም ይታወሳል፡፡

ኢሱና ዓብይ (ዶ/ር) ከሚሊኒየም አዳራሽ ንግግር የሚያደርጉበትን ልዩ የአቀባበል ምሽት ዝግጅት ማየትን ብዙዎች አስቀድመው ነበር፡፡ ‹‹ኳሱን ዝጉልንና የሚሊኒየም አዳራሽን ዝግጅት እንይ›› እስኪባል ድረስ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰላም ማውረድ ትልቅ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት በመካከላቸው የነበረውን ጠላትነት አስወግደው ፣ ኤርትራዊያን ወይም ኢትዮጵያዊያን ብቻ አልነበሩም በታላቅ ሐሴትና ደስታ የተቀበሉት፡፡ ጉዳዩን የዓለም ማኅበረተሰብም በቸልታ ሊያልፈው አልፈለገም ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) የኢትዮ አርትራ ግንኙነትን ለማሻሻል ለወሰዱት ተነሳሽነት ታላቅ ክብር ጎረፈላቸው፡፡ ከክብርም ባለፈ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ተሰጣቸው፡፡

የጀርመኖች የሄሰን ሰላም ሽልማት ለዓብይ (ዶ/ር) የተበረከተበት አንዱ ምክንያትም፣ ይኼው የኢትዮ ኤርትራ ዕርቀ ሰላም ጉዳይ ነበር፡፡

የኤርትራና የኢትዮጵያ መታረቅ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ጉርብትና እንደሚያሸጋግረው ትልቅ ተስፋ አሳድሮ ነበር፡፡ በጊዜው ዕርቀ ሰላሙም ሆነ ዳግም ግንኙነቱ በመርህ ላይ ይመሥረት የሚል ውትወታ ያደረጉ እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡

በ2011 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ተነግሮ ነበር፡፡ በሳዑዲው ንጉሥ ሳልማን ጥሪ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በተገኙበት፣ ታላቅ የሰላም ሜዳሊያ ሁለቱ መሪዎች ሲሸለሙም ታይቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ መሪዎቹ ፈረሙት ተብሎ ይፋ የወጣው ‹‹የጅዳው ሰላም ስምምነት›› ሰነድ እጅግ ውስን ነጥቦች ብቻ የተቀመጡበትና ጥቅል ይዘት ያለው መሆኑ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር፡፡

ከወራት ቀደም ብሎ በግንቦት 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ሲደረግ የአልጀርሱን ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀበለው የሚያረጋግጥ መግለጫ ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ወደ 100 ሺሕ ሰዎች ያስጨረሰ ደም አፋሳሽ ጦርነት በተደረገ ማግሥት ነበር የአልጀርስ ስምምነት የተፈራረሙት፡፡

የድንበር ግጭቱን በሄግ የግልግል ፍርድ ቤት ለመፍታት በተስማሙበት መሠረትም፣ ይገባኛል የሚሉት መሬት ጉዳይ ይግባኝ በሌለው የፍርድ ቤት ውሳኔ ዕልባት ተሰጥቶትም ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በድንበሩ አከላለል ላይ በነበራት ቅሬታ ሳቢያ ወሰኑን የማስመርና ድንበሩን የማካለሉ ሥራ ሳይካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም በሁለቱ አገሮች ድንበር መካከል ውጥረት እንደነገሠ ሰላምም ሆነ ጦርነት ሳይኖር ለመዝለቅ ተገደዋል፡፡

ይህ ሁሉ ታልፎ የዓብይ (ዶ/ር) እና የኢሳያስ ግንኙነት መልካም መሆን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ለቆዩ ነባር የውዝግብ ምንጮችና ችግሮች መፈታት ትልቅ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡

በሁለቱ መሪዎች መካከል መልካም ግንኙነት መመሥረቱን ተከትሎ የሁለቱ አገሮች ድንበር ለንግድ ግንኙነት ክፍት ሆኖ ነበር፡፡ በዚያ ሰሞን በመቀሌ ከተማ መናኸሪያ ‹‹አስመራ የሞላ›› የሚል የትራንስፖርት መጓጓዣ አገልግሎት ጥሪ መደመጥ ጀምሮ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደገና በረራ መጀመሩ ደግሞ ከመሀል አገር ጋር የሚደረገውን ግንኙነትም የበለጠ ያጠናከረ አጋጣሚ ሆኖ ነበር፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትን በተመለከተ በዚያ ሰሞን የታዩ የለውጥ ዕርምጃዎች የአገሮቹ መልካም ግንኙነት በቀጣይ ዓመታት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ግምት ያሳደረ ነበር፡፡ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ባሉበት ኢሳያስና ዓብይ (ዶ/ር) የአገሮቹን ድንበር ዳግም እንዲከፈት ካደረጉበት አጋጣሚ ጀምሮ፣ በንግድም ሆነ በሌላ መንገዶች ብዙ ለውጦች ታይተው ነበር፡፡

በድምፃዊ ኪሮስ የሙዚቃ ግጥም ‹‹መሰንበት ደጉ ብዙ ያሳያል›› እንደተባለው ሁሉ ለ20 ዓመታት በጠብ ሲፈላለጉ በኖሩት ጎረቤታሞች መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ አስገራሚ የግንኙነት ለውጦች ነበር የታዩት፡፡

የትግራይ ክልል የወቅቱ ፕሬዚዳንት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በጉዳዩ ተገርመው የዓብይ (ዶ/ር) ድፍረትን እስኪያደንቁ ድረስ ተአምራዊ የሆኑ የግንኙነት ለውጦች መምጣታቸው አይዘነጋም፡፡ የአሁኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ያን ለውጥ የዓብይ (ዶ/ር) ደፋር ዕርምጃ የፈጠረው አጋጣሚ ስለመሆኑ አንድ ወቅት ላይ ተናግረውት ነበር፡፡

ነገር ግን በሒደት ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት የመመለስ አዝማሚያ መያዝ ጀመረ፡፡ የዓብይ (ዶ/ር) እና የኢሳያስ መቀራረብ በሒደት ትግራይን የመክበብ ሴራ መባል ጀመረ፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ መታረቅ፣ እንዲሁም እንደገና መቀራረብ ትግራይን ለመውጋት የተጀመረ ጥረት ስለመሆኑ በትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን በኩል በሰፊው መነገር ጀመረ፡፡

ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን ዳግም መጠቀም ልችጀምር ነው፣ እንዲሁም ከጂቡቲ ወደብ ጥገኝነት ነፃ ልትወጣ ነው የሚል ተስፋ ፈጥሮ የነበረው የግንኙነት መሻሻል በተጠበቀው ልክ አዎንታዊ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችል ቀረ፡፡ በኢትዮጵያ የተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ግራ ወደ የሚያጋባ ቅርቃር ውስጥ እንደከተተው ይነገራል፡፡

የኤርትራ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆኑ በኢትዮጵያ መከፋፈል የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አንዳንዶች የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል በተፈጸሙ ሰብዓዊ ፍጅቶች በቀጥታ ተሳታፊ ስለመሆኑ ይወነጅሉታል፡፡ ምዕራባዊያኑም ቢሆን ኤርትራ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን፣ ከፍተኛ የሰብዓዊና የጦር ወንጀሎች ፈጽማለች የሚለውን አቋም በሰፊው ሲያራምዱት ነበር፡፡

የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር በኃይል ተቆጣጥረዋል የሚለው ጉዳይም እስካሁን ዕልባት ያላገኘና ተደጋግሞ የሚነሳ ነው፡፡ የኤርትራ ኃይሎች ከያዙት የኢትዮጵያ ድንበር ለቀው ይውጡ የሚለው ነጥብ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንዱ አካል እስከመሆን የደረሰ ነው፡፡

በሌላ በኩል ሕወሓት ራሱ የከፈተውን ጦርነት ቀጣናዊ ለማድረግና የኤርትራ ኃይሎችን ተሳታፊ ለማድረግ ሮኬት ወደ አስመራ መተኮሱን የችግሩ ምንጭ ብለው የሚያወሱ ወገኖች አሉ፡፡ የኤርትራ ሠራዊት በሕወሓት ትንኮሳ ተገዶ ወደ ጦርነቱ መግባቱን የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች፣ ኤርትራም ቢሆን ራሷን ከጥቃት የመከላከል መብት ያላት ሉዓላዊት አገር እንደሆነች ሲከራከሩ ነበር፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ያለፉት አምስት ዓመታት ግንኙነት ከጦርነቱ በፊት፣ በጦርነቱ ወቅትና ከጦርነቱ በኋላ በሚሉ የተለያዩ ምዕራፎች የሚገለጽ ባህሪ እንዳለው ግሪጎሪ ኮፕሌ የተባሉ ጸሐፊ በቅርብ ጊዜ ጽሑፍቸው ይጠቅሳሉ፡፡ “Has the west already lost control of its most vital sea route?” በሚል ርዕስ የቀረበው ጽሑፍ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን ብቻ ሳይሆን ቀጣናዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችንም በሰፊው ያስተነትናል፡፡

‹‹የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጦርነቱ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  አህመድ (ዶ/ር) ወዳጅ ነበሩ፡፡ በጦርነቱ ወቅት ደግሞ ሕወሓትን በመውጋት ሒደት ሁለቱ መሪዎች አጋር ሆኑ፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሯል፤›› ሲል ጽሑፉ ያስታውሳል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና የተቋጨበት መንገድ (የሰላም ስምምነቱ) በኢትዮጵያ የተለየ የኃይል አሠላለፍ እንዳስከተለ ጸሐፊው ያወሳሉ፡፡ የኤርትራ መንግሥትም ይህን የኃይል አሠላለፍ በተከተለ ሁኔታ የግንኙነት አቅጣጫውን መቀየሱን በግልጽ ያነሱታል፡፡

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በኋላ የኤርትራ ጂኦ ፖለቲካ ገበያ መድራቱን ይኼው ጽሑፍ ያትታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በቀጣናው እጅግ ተፈላጊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ያነሳል፡፡ ከቻይና እስከ ሩሲያ እንዲሁም የባህረ ሰላጤው አገሮች ከኤርትራ ጋር የተሻለ ግንኙነት የመመሥረት ሩጫ ላይ መሆናቸውን ያተተው ዘገባው፣ ይህ ደግሞ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ቅኝትን የሚወስን ተፅዕኖ እንዳለው ነው በሰፊው የዘረዘረው፡፡

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪው ክንደያ ገብረ ሕይወት (ፕሮፌሰር) በቅርቡ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን በመሬት የተነሳ ዳግም ወደ ግጭት አይገቡም፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት በመርህ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደተቀበለው ገልጸው፣ ‹‹ጉዳዩ የመሬት ሳይሆን የሕዝብ ነው፤›› በማለት ጠቅሰዋል፡፡

የድንበር ውሳኔው ይተግበር ቢባል መቃብርን፣ ቤትን፣ የእምነት ተቋማትን ሁሉ የሚከፍል መሆኑን ያስረዱት ክንደያ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የድንበር ጉዳይ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ሊፈታው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ዛላምበሳ ከተማን ለሁለት ከፍሎ መንገድ የመሥራት እንቅስቃሴ በኤርትራ በኩል መኖሩን ጠቁመው፣ ያም ቢሆን ችግሩ በፌዴራል መንግሥት በኩል ይፈታል የሚል እምነት እንዳለ አክለዋል፡፡

‹‹የኤርትራ ኃይሎች ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት ቦታ የመመለሳቸው ጉዳይ በስምምነቱ መሠረት አማራጭ አይደለም፤›› ሲሉ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ የአገር ድንበር የማስከበር ጉዳይ የፌዴራል መንግሥቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከኤርትራም ሆነ ከማንም ጋር ያለውን ችግር ‹‹በሰላም ቢፈታ ነው የምንመርጠው፤›› ሲሉም ሐሳባቸውን ደምድመዋል፡፡