July 24, 2023 – Konjit Sitotaw
የጠየቁትን ያህል ጉቦ ያልሰጣቸውን አንድ አሽከርካሪ የትራፊክ ፖሊሶች በጥይት ደብድበው መግደላቸው ተሰምቷል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የትራፊክ ፖሊስ አባላት የጠየቁትን ጉቦ አልሰጠም ያሉትን አንድ አሽከርካሪ በጥይት ደብድበው መግደላቸውን የሟች ቤተሰቦች እና የሥራ ባልደረቦች ገልጸዋል። ሟች ሳሙኤል መረተ የ33 ዓመት ዕድሜ ያለው ሲሆን ከአዲስ አበባ ቡታጅራ መስመር በአሽከርካሪነት ይሰራ ነበር።
ሳሙኤል በመስመሩ በሰበብ አስባቡ ካልቀጣንህ የሚሉትን የትራፊክ ፖሊስ አባላት ለማባበል ዝርዝር የሃምሳ ብር ኖቶችን በእጃቸው እያስጨበጠ ማለፍ የሁልጊዜ ተግባሩ እንደነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡
የሳሙኤል ረዳት ሆኜ ሥሠራ ነበር የሚለው አንዱዓለም ሁሴን ለዶቼ ቬለ እንደተናገረው፦
መንገደኞችን አሳፍረው ከአዲስ አበባ ቡታጅራ በመጓዝ ላይ እንዳሉ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ላይ ሲደርሱ ሦስት ትራፊኮች እንዳስቆሟቸው ይናገራል፡፡
ሟች ሳሙኤል የመውጫ ወረቀት እና ሃምሳ ብር ሲሰጥ ከትራፊኮቹ አንዱ ሀምሳውን ቀይረህ መቶ አድርግ ሲለው መስማቱንም ያስታውሳል።
“ . . . ሟቹም አሁን የለኝም አልተዘጋጀሁም ሲለው ትራፊኩም አለበለዚያ የተሸከርካሪውን ሠሌዳ እፈታለሁ በማለት ሟችን በቦክስ መታው፡፡ ይሄኔ በንዴት ተሽከርካሪውን አስነስተን ወደፊት መሄድ ስንጀምር ተከትለው መተኮስ ጀመሩ፡፡
ጥቂት እንደተጓዝን ተሸከርካሪውን በማቆም እኔም ሆንኩ ሌሎች መንገደኞች ደንግጠን ወረደን መሮጥ ጀመርን ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እሱን በጥይት መትተው ጣሉት “ ሲል ገልጿል፡፡
የሟች ሳሙኤል አባት አቶ መረተ ለማ
ከትራፊክ ፖሊስ አባላቱ ጋር አለመግባባቱ የተነሳው በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ላይ ቢሆንም ግድያው የተፈጸመው ግን በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ሱተን ዙሪያ ቀበሌ ድረስ ተከታትለው በመምጣት አንደሆነ አባት ገልጸው ” ይህን ለማን አቤት ልበል ? “ ሲሉ ይጠይቃሉ።
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የተሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ፈይሳ ደበላ በጉዳዩ ላይ የሰጡት ምላሽ፦
ወንጀሉ የተፈጸመው እሳቸው ከሚመሩበት የተሬ ወረዳ አልፎ ጉራጌ ዞን ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ “ በዚህ ላይ እኔ የምላችሁ ነገር የለም፡፡ ባይሆን የደቡብ ክልል ፖሊስን ጠይቁ “ ብለዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሀመድ ምላሽ፦
የወንጀሉ አድራሾች በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ናቸው ያሉ ሲሆን ድርጊቱን በመፈጸም የተጠረጠሩ ሦስት የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አክለውም፥ “ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ወዲያው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡ አሁን ምርመራውን ከኦሮሚያ ክልል የሥራ ሃላፊዎች ጋር አብረን እየሠራን እንገኛለን ፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በጉራጌ ዞን ውስጥ በመሆኑ ምርመራውን ወደ ዞኑ ለማዛወር በሂደት ላይ ነው ያለነው “ ብለዋል፡፡
ዘገባው የዶይቼ ቬለ ነው።