
እናት ፓርቲ
የፌዴራል መንግሥት፣ የትግራይና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ የሚያደርጉት ግልጽና ስውር እንቅስቃሴ ይቅርታ የማያሰጥ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ነው!
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
ኢትዮጵያን አጽንተው ካቆዩና ካቆሙ ተቋማት ከመንግሥታዊ ሥርዓት ባልተናነሰ ሁኔታ የሃይማኖት ተቋማት በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለአገራችን ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ትልቅ ባለውለታ ናት። ይሁን እንጂ መንግሥት ሕዝባችንን ለመለያየት በተጠና መልኩ እየተገበረ ያለውን የጎሳ ፖለቲካ ትርክት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በማስረጽና በመጫን የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ሰባኪ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ከፋፋዮችን ደግፎ በማሰማራትና ለእኩይ አላማቸው ማስፈጸሚያ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ በእጅ አዙር ቤተ ክርስቲያኗ እንደ ተቋም ጸንታ እንዳትቆም ጉልህ የሆነ የማፍረስ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
ከወራት በፊት “የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” በሚል በኦሮሚያ ክልል በትላንትናው ቀን ደግሞ “መንበረ ሰላማ” በሚል “የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ፈጸምን” የተባለበት ሁኔታ የዚሁ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማፍረስ ሴራ መገለጫዎች ናቸው። በዚህ እኩይ ተግባር ቀደም ሲል የጠቀስናቸው የፌዴራል መንግሥቱ፣ የኦሮሚያ ክልልና የትግራይ ክልል መንግሥታት ከድርጊቱ ፊታውራሪዎች ባልተናነስ እኩል ተጠያቂነት አለባቸው።
እናት ፓርቲ እንደ ወግና ሥርዓት ጠባቂ የፓለቲካ ፓርቲ በእምነት ተቋማት ላይ የሚቃጣ ጥቃትና የሚደረግ ሴራ አገርን የማፍረስ ተልእኮ አካል እንደሆነ በጽኑ ያምናል፤ አጥብቆም ይኮንናል። የእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተቋም አፍራሽና አገር አፍራሽ ተግባራትን ክፉ ፍሬና ውጤት መመልከቻው እሩቅ ሳይሆን በአጭር ጊዜ የሚታይ፣ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ታሪክ በክፉ የሚመዘግበውና የሚያወሳው ጉዳይ ይሆናል።
በትግራይ ባሉ አባቶች “መንበረ ሰላማ” ከመሰየም ጀምሮ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ የሰላምና የውይይት ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። ቀደም ሲል “የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” በሚል በኦሮሚያ መንግስት ጣልቃ ገብነት ሲከናወን የነበረው ህገ-ወጥ ሲመት ለብዙ ምዕመናን ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ነበር። መንግስት በጉዳዩ ላይ እንደሌለበት ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በአስታራቂነት ሲተውኑ ማየታችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። አሁን ደግሞ የብፁአን አባቶችን “የአሸማግሉን” ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው የብልጽግና ፓርቲ መራሹ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የታላቋ ሀገረ ትግራይ ምስረታ ሰለባ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ በግልጽ እየተወጣ ይገኛል።
ስለሆነም፤
፩. የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን በእነርሱው አይዞህ ባይነት እየተከናወነ ያለውን የጥፋት ጉዞ ወደ ትክክለኛ መንገድ በማምጣት ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤
፪. ቅዱስ ሲኖዶስ በኦሮሚያ ክልል በምእመናን ላይ የደረሰ ሞትና የአካል ጉዳት በማይደርስበት ኹኔታና ትዕግስት በተላበሰና አስተማሪ በሆነ መልኩ ችግሩ የሚፈታበትን ዘዴ በማበጀት የቤተክርስቲያኒቱን ልእልና እንዲያስከብር፤
፫. የእምነቱ ተከታይ ምእመናንም ይህን ተከትሎ በተሰማቸው የሀዘን ስሜት አፍራሽ ወደ ሆነ አቅጣጫ ከማምራት እንዲቆጠቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ሐምሌ ፲፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.