
25 ሀምሌ 2023, 08:22 EAT
በአሜሪካ የተራዘመው ሙቀት በርካታ ሰዎች የጋለ ቁስ በመንካታቸው እየተቃጠሉ ወደ ሆስፒታል እንዲመጡ እንዳደረጋቸው ተዘገበ።
አንዳንድ የአሪዞና የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት አንዳንድ ታካሚዎች የጋለ አስፋልት ላይ ወድቀው በመቃጠላቸው ለሕክምና ይመጣሉ።
ፊኒክስ የተሰኘችው ከተማ እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ 43 ዲግሪ ሴልሺየስ የደረሰ ሙቀት ለሁለት ተከታታይ ቀናት አይታለች።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከመሬት የሚመነጨው ሙቀት ውሃ ሊያፈላ ትንሽ የቀረው ነው።
የአሪዞና የቃጠሎ ማዕከል ሠራተኛ የሆኑት ዶክተር ኬቪን ፎስተር ለቢቢሲ እንደሚናገሩት የሆስፒታሉ 45 አልጋዎች አሁን ታካሚዎችን በማገዝ ላይ ናቸው።
ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ታካሚዎች አንድ ሶስተኛው ኮንክሪትና አስፋልት ያቃጠላቸው መሆናቸውንም ጨምረው ይገልጣሉ።
“እርግጥ ነው ለወትሮው ሞቃታማው ጊዜ ቃጠሎ አለ። ነገር ግን የዘንድሮው ከጠበቅነው በላይ ነው” ብለዋል።
ገና ሞቃታማው ጊዜ ሳይጋመስ ባለፈው ዓመት በቃጠሎ ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ታካሚዎች ቁጥር በላይ መመልከታቸውንም ይናገራሉ።
አብዛኛዎቹ ታካሚዎች በሙቀቱ ምክንያት መቆም ተስኗቸው የወደቁ ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች አሊያም ከወደቁ በኋላ ቶሎ ብድግ ያላሉ ሕፃናት ናቸው።
- በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ መካከል አዲስ ውቅያኖስ እየተፈጠረ ይሆን?6 ሀምሌ 2023
- የኢትዮጵያ የቡና ገበያ የውጭ ንግድ ውጣ ውረዶች25 ሀምሌ 2023
- ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ‘ጃ’ በዓለም አቀፉ ምናብ23 ሀምሌ 2023
ነገር ግን “ትልቁ ችግር” መንገድ ላይ በውሃ ጥማት ምክንያት ወድቀው የሚገኙ አደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎች ናቸው።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 150 ታካሚዎች ከውጭ ሆነው እንዲታከሙ እያገዘ ሲሆን በርካታ ታካሚዎች ብረታብረት በመንካት የተቃጠሉ ናቸው።
የመኪናዎች ውስጠኛው አካልና ጥቁር የሆነው የአስፋልት ክፍል ሙቀት የማመቅ ኃይል ስላለው አደገኛ እንደሆነ ሙያተኞች ይጠቁማሉ።
ለጥቂት ሰከንዶች እንኳ ቢሆን ብረታ ብረት አሊያም አስፋልት መንካት ቃጠሎ ሊያስከትል ይችላል።
ሆት ሪሊፍ ኔትዎርክ አሪዞና የተባሉ ተቋም 235 የቅዝቃዜና ፈሳሽ ማግኛ ጣቢያዎችን በግዛቲቱ ተክሏል።
ተጠቃሚዎች ወደ ጣቢያዎቹ ሄደው በሰው ሠራሽ አየር ማጤዣና በውሃ ራሳቸውን አክመው መመለስ ይችላሉ።
አብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች ቤት የሌላቸው ቢሆኑም አንዳንድ ሰዎች ቀኑን ሙሉ የቤታቸውን አየር ማጤዣ አብርተው የመዋል አቅም ስለሌላቸው ወደጣቢያው እንደሚመጡ ክሌዎ ዋርነር ትናገራለች።
ሁሉም የማቀዝቀዣ ጣቢያዎች በበጎ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚንቀሳቀሱ ሲሆኑ ክፍት ቦታዎችን አሊያም የእምነት ሥፍራዎችን ነው የሚጠቀሙት።
ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎች መጥተው በሞቃታማ ሰዓታት በሥፍራው እንቅልፍ ወስደው እንዲሄዱ ማድረግ ጀምሯል።
ማሕበረሰቡ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አሁን 18 ገደማ የማረፊያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ክሌዎ ታስረዳለች።
አንድ የ73 ዓመት የአሜሪካ አየር ኃይል ጡረተኛ አውቶብስ መጠበቂያ የብረት ጥላ ውስጥ ገብተው ሲቀመጡ የደረሰባቸው ቃጠሎ ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል።
“ሙቀት አዲሴ አይደለም። ፊሊፒንስ ለሰባት ዓመታት ኖሪያለሁ። እንዲህ ዓይነት ሙቀት ግን አይቼ አላውቅም” ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።