የእስራኤል ተቃውሞ

25 ሀምሌ 2023, 08:31 EAT

የእስራኤል ፓርላማ የአገሪቱን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ስልጣን የሚገድብ አወዛጋቢ ህግ ማጽደቁን ተከትሎ አገሪቷ በተቃውሞ እየተናወጠች ነው።

የእስራኤል ፖሊሶች ትናንት አመሻሹ ላይ በአደባባይ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ከወጡ በርካቶች ጋር ተጋጭተዋል።

በርካታ ማሻሻያዎችን የያዘው ይህ ውሳኔ ፍርድ ቤቱ ምክንያታዊ አይደሉም ብሎ የሚያስባቸውን የመንግሥት ውሳኔዎች እንዳይሽር ይከለክላል።

በእየሩሳሌም እና በቴልአቪቭ የሚገኙ ጎዳናዎች በተቃዋሚዎች የተዘጉ ሲሆን ፖሊስም ውሃ በመርጨት ለመበተን ሞክሯል።

የቀኝ አክራሪው መንግሥት ያደረገው ይህ ማሻሻያ የእስራኤልን ዲሞክራሲ አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነም ተቺዎች እየተናገሩ ነው።

የፍትህ ማሻሻያው እንደሚደረግ ከተሰማ በኋላ በርካቶች ለወራት ያህል ተቃውሟቸውን አደባባይ እያሰሙም ነበር።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ያስተላለፈው ውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚነን ኔታንያሁ ከፍተኛ ድል ተደርጎም ተወስዷል።

ነገር ግን ትግሉ አላላቀም፤ ገና ለወራት ሊቀጥል ይችላል እየተባለ ነው።

መንግሥትን የሚቆጣጠር ቡድን እና የመሃል ተቃዋሚው መሪ ያየር ላፒር አዲሱ ህግ እንዲሻር ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን እንናቀርባለን ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የእስራኤል ሂስታድሩት የሰራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ መምታት እንደሚጠራም አስጠንቅቋል።

የአየር ኃይል አብራሪዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠባባቂዎች ህጉ ወደ ስራ ከገባ ለስራ ሪፖርት እንደማያደርጉም ተናግረዋል።

ለማንኛውም ዓይነት ስጋት ፈጣን ምላሽ እሰጠላሁ በማለት ለምትኩራራው እስራኤል ይህ ሁኔታ የአገሪቱን የደህንት ሁኔታ ሊያደፈርስ ይችላል የሚል ጭንቀትን ፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በበኩላቸው መንግሥት “አብዛኛውን የአገሪቱን ዜጎች ውሳኔ መሰረት ባደረጉ ፖሊሶች እንዲያከናውን” ህጉ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

እስራኤል ያቀደቻቸው እነዚህ የፍትህ ማሻሻያዎች በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ታላላቅ ተቃውሞዎችን አስነስቷል። ሰኞ ዕለት ቢያንስ 22 ተቃዋሚዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ተቃዋሚዎች ይህ ለውጥ የአገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚያዳክምና ወደ ጨቋኝ ስርዓትም ሊከታት ይችላልም በሚል ስጋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።