
ከ 7 ሰአት በፊት
የጋናዋ ሚኒስትር በቤታቸው ውስጥ ዘረፋ ተፈጽሞብኛል ብለው ለፖሊስ ሪፖርት አደረጉ።
ነገር ግን ጉዳዩ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተቀልብሶ ራሳቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ሚኒስትሯ ሴሲሊያ አቤና ዳፓህ ባለፈው ሃሙስ ከቤታቸቸው ተዘረፈ ብለው ሪፖርት ያደረጉት መጠን ከፍተኛ መሆኑንም የፍርድ ቤቱ የክስ መዝገብ ያስረዳል።
በዚህም መሰረት 1 ሚሊዮን ዶላር፣ 300 ሺህ ዩሮ፣ እንዲሁም 35 ሺህ ዶላር የሚሆን የጋና 350 ሺህ ሲዲ ከቤታቸው እንደተዘረፈ የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
በተጨማሪም 35 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የእጅ ቦርሳዎች እና 95 ሺህ ዶላር የሚያወጡ ጌጣጌጦች ከቤታቸው መዘረፉንም ጨምሮ ያትታል።
የ68 አመቷ ሚኒስትር በፍርድ ቤቱ የክስ መዝገብ ላይ በተጠቀሱ አሃዞች ላይ ቢከራከሩም ነገር ግን ይህንን ያህል ገንዘብ ሚኒስትሯ ነበራቸው መባሉ በርካታ ጋናውያንን አስቆጥቷል።
የአገሪቱ ምንዛሪ ከዶላር ጋር ሲነጻጻር በፍጥነት እያሽቆለቆለ መጥቷል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት ለዚህም ተጠያቂ ያደረጉት ዶላር አከማችተው ተቀምጠዋል ያሉ አካላትን ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ አንድ የመንግሥት ሚኒስትር ራሳቸው ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ አገራት ገንዘቦች ይዘው መገኘታቸው በርካቶችን አስደንግጧል።
የንጽህና እና የውሃ ሃብት ሚኒስትር የሆኑት ሴሲሊያ ላለፉት አምስት ዓመታት ከያዙት የኃላፊነት ቦታም ላይ በፈቃዳቸው መነሳታቸውን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት ከዚህ ስልጣን የለቀቁት የመንግሥት ስራን ላለማስተጓጎል ነው። ማንኛውም አይነት ምርመራ በቅንነትና በታማኝነት መስራታቸውን እንደሚያሳይ እርግጠኛ መሆናቸውን አክለው ተናግረዋል።
ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው በአገሪቱ የተነሳውን ቁጣ አላበረደውም። ሰኞ እለትም ሚኒስትሯ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የከፍተኛ ባለስልጣናትን የዝርፊያና ሙስና የሚመለከተው የልዩ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ሚኒስትሯ “ከመኖሪያ ቤቷ ተዘርፏል በተባለው ከፍተኛ ገንዘብ እና ሌሎች ውድ ዕቃዎችን በተመለከተ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውም” በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
ይህ ሁሉ ውዝግብ የተጀመረው ሚኒስትሯ ከባለቤታቸው እና ልጃቸው ጋር በዋናዋ ከተማዋ አክራ መኖሪያቸው ላይ በተፈጸሙ ተከታታይ ዘረፋዎች ጋር የተያያዘ ነው።
እነዚህን ተከታታይ ዘረፋዎች በመፈጸም የተጠረጠሩት ሁለት የቤት ሰራተኞቻቸው ናቸው።
አንደኛዋ ሰዎች መምጣት አለመምጣታቸውን እየጠበቀች የነበረች ሲሆን ሌላኛዋ ደግሞ ገንዘቡንና ሌሎች ጌጦችን ዘርፋለች።
ሁለቱ ተጠርጣሪ የቤት ሰራተኞችና ሶስት ተባባሪዎቻቸው በክሱ ላይ አስተያየት አልሰጡም ።
- ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ‘ጃ’ በዓለም አቀፉ ምናብ23 ሀምሌ 2023
- ሩሲያ ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ይላክ የነበረውን እህል መተካት እንደምትችል ፑቲን አስታወቁ25 ሀምሌ 2023
- የኢትዮጵያ የቡና ገበያ የውጭ ንግድ ውጣ ውረዶች25 ሀምሌ 2023
ከክሱ ጋር የተያያዘው የምርመራ ሪፖርት እንደሚያሳየው ጥቅምት ወር ላይ የሚኒስትሯ ባለቤት ዳንኤል ኦሴይ ክፉር ወደ ቤታቸው በሚገቡበት ወቅት ከመኝታ ክፍላቸው ያልተለመደ ድምጽ መስማታቸውን ነው።
ከተከሳሶቿ አንዷ ከመኝታ ክፍሉ ጀርባ ተደብቃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ከዚያም ገንዘብና ሌሎች ጌጦች እንደጠፉ ጥንዶቹ የተረዱ ሲሆን ለፖሊስ ሪፖርት ያደረጉት ከሰባት ወራት በኋላ ነው።
ሚኒስትሯ ለፖሊስ ሪፖርት ለማድረግ ለምን ይህንን ያህል ጊዜ እንደዘገየ ግልጽ ባይሆንም ተከሳቹ ዘርፈውታል የተባለውን ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ አውጥተውታል ተብሏል።
አንደኛዋ ተከሳሽ ከአክራ ወጣ ባለ ሶስት መኝታ ቤት እንዲሁም ፍሪጅ፣ ቴሌቪዥን፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ የጋዝ ማብሰያ እና የውሃ ማጣሪያ የመሳሰሉ የቤት ዕቃዎችን ጨምሮ ገዝታለች ተብሏል።
በተጨማሪ ለወንድ ጓደኛዋ ሀዩንዳይ ኢላንትራ እና ሆንዳ ሲቪክ የተሰኙ ሁለት መኪናዎችን ገንዘብ እንደሰጠችም ተነግሯል።
እነዚህ ጥንዶቹ በሌላ ከተማ ውስጥ ባለ ሶስታ መኝታ መኖሪያ ቤት እና የእቃ ማስቀመጫ መጋዘንም ተከራይተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ሌላኛዋ የሚኒስትሯ የቤት ሰራተኛ የነበረችው ግለሰብ ከዘረፈችው ገንዘብ የተወሰነውን ባለ ሶስት መኝታ ቤት ለመንባት ወጪ አድርጋለች ተብሏል።
ነገር ግን የተዘረፉት ሚኒስትር ይህንን ያህል ገንዘብ ከየት አገኙ? ምንጩስ የት ነው? የሚለው እንቆቅልሽ ሆኗል።
ሚኒስትሯ በስራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ “ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ገንዘቦች እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጋና የመገበያያ ገንዘብ በሆነው ሲዲ ተብሎ በሚዲያዎች የተገለጹ ዘገባዎች እኔና ባለቤቴ ለፖሊስ ሪፖርት ያደረግነውን በትክክል አይወክሉም” ብለዋል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ በሚኒስትሯ ላይ የተከፈተውን ምርመራ ሊያበላሽ ይችላል የተባለውን አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ የጸረ- ሙስና ዘመቻ ተሟጋቾችን ተስፋ አስቆርጠዋል።
“በመጨረሻም በኃላፊነት ቦታ ላይ እያለሽ ታማኝነትሽን የሚያረጋግጥ እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ ሲሉም ለሚኒስትሯ ደብዳቤ ጽፈዋል።
ሴሲሊያ ፕሬዚንት አኩፎ በአውሮፓውያኑ 2017 ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ መጀመሪያ ላይ በአቪየሽን ሚኒስትርነት በኋላም በጽዳትና ውሃ ሚኒስትርነት እያገለገሉም ነበር።
ሴሲሊያ በፕሬዚዳንቱ የሚኒስትር ካቢኔ ውስጥ ከነበሩት ሶስት ሴቶች አንዷ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ልዩ አቃቤ ህግ እንደዚህ በከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ቤታቸው ውስጥ መገኘቱን ማረጋገጥ እና ምንጩስ ከየት ነው? የሚለውን በሚመረምርበት ወቅት የሚኒስትሯ የወደፊት የፖለቲካ ዕጣ ፈንታቸው አደጋ ውስጥ ገብቷል።