ፑቲን ከአፍሪካ መሪዎች ጋር

25 ሀምሌ 2023, 07:49 EAT

ሩሲያ ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ይላክ የነበረውን የእህል ወጪ ንግድ መተካት እንደምትችል ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።

ከዩክሬን ወደ አፍሪካም ሆነ ሌሎች አገራት እህል ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ በጥቁር ባህር መተላለፍ ይችል ዘንድ ከተደረሰው ስምምነት ሩሲያ መውጣቷን ካሳወቀች በኋላ ነው ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት።

ከቤተ መንግሥታቸው ክሬምሊን በወጣው መግለጫ መሰረት አገራቸው ለአፍሪካ ይላክ የነበረውን እህል ያለ ክፍያ የማጓጓዝ አቅም አላት ብለዋል።

ባለፈው ዓመት እስከ ከጥር እስከ ሰኔ ወር ድረስ ሩሲያ 10.8 ሚሊዮን ቶን ስንዴ በመላክ ለአፍሪካ ትልቁ የስንዴ አቅራቢ ነበረች።

በዚሁ ወቅት ከዩክሬን በወጪ ንግድ ለአህጉሪቱ የተላከው የስንዴ መጠን 6.3 ሚሊዮን ቶን መሆኑም ተገልጿል።

ሩሲያ በጎሮጎሳውያኑ 2023 አጋማሽ ድረስ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ እህል ወደ አፍሪካ መላክ መቻሏን አስረድተዋል።

ይህም በአገሪቷ ላይ በተጣለው እና ምርትን በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ለማቅረብ እጅጉኑ በሚጎዳው ማዕቀብ መካከል ነው ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ስለሚተላለፈው “የእህል ስምምነት” የተናገሩ ሲሆን ይህም የተነሳለት ዓላማው ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የረሃብ አደጋን መቀነስና በጣም ድሃ የሆኑትን የአፍሪካ፣ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ አገራትን መርዳት ነበር።

ሩሲያም እነዚህ ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ኃላፊነቷን ስትወጣ ነበር ብለዋል።

“ነገር ግን በምዕራባውያኑ ለአፍሪካ የሚጠቅም የበጎነት መገለጫ ተብሎ በተደጋጋሚ ቢጠቀስም እንደተባለው ሳይሆን ከዩክሬን ወጪ ንግድ በማድረግ ትላልቅ የአሜሪካና የአውሮፓ የንግድ ድርጅቶች ያለ ምንም እፍረት ኪሳቸውን ያደለቡበት ነው” ማለታቸው ሰፍሯል።

በዚህ ስምምነት መሰረት በአጠቃላይ 32.8 ሚሊዮን ቶን እህል ከዩክሬን መውጣት ቢችልም ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት ነው የተሸጠው።

እንደ ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ የመን እና አፍጋኒስታን ያሉ አገራት በዚህ ስምምነት ያገኙት 3 በመቶ ያነሰ ምርት ነው ብለዋል።

ሩሲያ በዘንድሮ የምርት ዓመት ዘመን ከፍተኛ ምርት ትጠብቃለች ብለዋል። አገሪቱ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ሁለተኛውን የሩሲያ- አፍሪካ ጉባኤ እንደምታስተናግድም አስታውሰዋል።

የጥቁር ባህር የእህል ስምምነት ማክተሙን በተመለከተ አባል አገራቱ በምግብ ዋጋ ንረት የተጎዱበት የአፍሪካ ህብረት እንዳሳዛነው መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ሩሲያ ኳታር እና ቱርክን በሚያካትተው እቅድ በኩል እህል ለማቅረብ እየገፋች ሲሆን አገራቱ ተቀብለውታል የሚለው እስካሁን ግልጽ አይደለም።