ዮርዳኖስ እና እናቷ በምርቃቷ ዕለት ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ዮርዳኖስ እና እናቷ በምርቃቷ ዕለት ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር

25 ሀምሌ 2023

ዮርዳኖስ ወሮታው ሴሬብራል ፓልሲ በተባለ የጤና እክል ምክንያት ከልጅነቷ ጀምሮ እጅ እና እግሯን በፈቃዷ ማዘዝ፣ ሚዛኗን መጠበቅ እንዲሁም ለመናገርም ትቸገራለች። ልዩ እገዛ የሚያስፈልጋት ተማሪ ናት።

ዮርዳኖስ ከመዋዕለ ሕጻናት ጀምሮ ሞግዚቶች አብረዋት ክፍል ውስጥ በመቀመጥ ድጋፍ እያደረጉላት ነው ትምህርቷን የተከታተለችው።

ይህ ሁኔታ ግን ከስኬት አላገዳትም። ባለፈችባቸው የትምህርት ደረጃዎች ውጤታማ በመሆን ለከፍተኛ ትምህርት በቅታለች።

የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪን 91.3 በመቶ፣ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዋን 3.8 እንዲሁም 458 የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት በማምጣት ነበር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀለችው።

ላስመዘገበቻቸው ከፍተኛ ውጤቶችም ከእርሷ ጉብዝና በተጨማሪ የቤተሰብ “የትችያለሽ” ምክር ብርታት እንደሆናት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እናቷ ወ/ሮ እህተ ይናገራሉ።

“በአካባቢያችን የነበሩ መዋዕለ ሕጻናት አንቀበልም ብለውን ከዓለም ባንክ ወደ ካዛንቺስ ወስደናት ነው የተማረችው” ይላሉ ወ/ሮ እህተ።

ዮርዳኖስ ትምህርቷን በመኖሪያ ሰፈሯ አቅራቢያ በሚገኝ ትምህርት ቤት መከታተል የጀመረችው የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርትን (ኬጂ) ከጨረሰች በኋላ ነው።

ወደ ትምህርት ቤት የምትሄደው ከሞግዚቶቿ ጋር በመሆን ነው። ይህም በአንድ ወቅት ጥርጣሬን ፈጥሮ ጥያቄ አስነስቶባት ነበር።

በትጋት ትምህርቷ በመከታተል ያላትን ውጤት በማሻሻል ከክፍሏ ሦስተኛ ደረጃን በያዘችበት ጊዜ፣ የትምህርት ቤቷ ርዕሰ መምህር ውጤቱ የእሷ ሳይሆን የሞግዚቶቿ ሊሆን ይችላል በማለት ውድቅ ያደርግባትል።

ልጃቸውን በማገዝ እና በማበረታታት በራሷ ውጤታማ መሆን እንደምትችል ድጋፍ የሚሰጧት ቤተሰቦቿ የርዕሰ መምህሩን ውሳኔ በመቃወም፣ በዮርዳኖስ ችሎታ ካላቸው እምነት የተነሳ ራሱ እንዲፈትናት ጠይቀው በድጋሚ ፈተናው ተሰጣት።

ነገር ግን ውጤቱ ርዕሰ መምህሩ ከገመተው ውጪ ሆኖ የዮርዳኖስን ብቃት እራሱ ለማረጋገጥ ቻለ። በቀደመው ውሳኔው ስህተት መስራቱን ያመነው ርዕሰ መምህሩ ዮርዳኖስን እና ቤተሰቧን ይቅርታ በመጠየቅ ትምህርቷን እንድትቀጥል መፍቀዱን እናቷ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዮርዳኖስ ትምህርቷን በዚህ ሁኔታ እየቀጠለች ሳለ ካለችበት አካላዊ ሁኔታ አንጻር አምስተኛ ክፍል ስትደርስ ፎቅ የሌለበት ትምህርት ቤት ተፈልጎ እንድትመዘገብ ተደረገ።

“ነገር ግን ያገኘነው ትምህርት ቤት አንቀበልም አለን። ውጤቱን ስናሳያቸው እነሱም የእርሷ አይደለም፣ ሞግዚቶቿ የሠሩት ነው አሉን” ይላሉ እናት ወ/ሮ እህተ።

ነገር ግን አሁንም እንደገና እንድትፈተን ትምህርት ቤቱ ጠየቀ። ዮርዳኖስ አሁንም ፈተናውን ወሰደች። እንደተለመደው በጥሩ ውጤት አለፈች።

የዮርዳኖስ እናት ወ/ሮ እህተ
የምስሉ መግለጫ,የዮርዳኖስ እናት ወ/ሮ እህተ

ዮርዳኖስ ባለባት የጤና እክል ምክንያት ድጋፍ የሚያደርጉላት ሞግዚቶች ሙሉ ሰዓታቸውን ሰጥተው አብረዋት ይሆናሉ። በክፍል ውስጥ ስትማር፣ ስትመገብ፣ ወደ መጸዳጃ ቤት ስትሄድ ሁሉ ከጎኗ አይለዩም።

ነገር ግን በክፍል ውስጥ የሚሰጣትን ትምህርት በትኩረት ትከታተላለች፣ የሚሰጧትን የክፍል እና የቤት ሥራዎች በእራሷ ትሠራለች፣ ያለመሰልቸት ታጠናለች እንዲሁም ፈተናዋን ካለማንም እርዳታ ትሰራለች። በዚህ ጉዞዋም ስኬታማ ናት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የቤተሰብ ድጋፍ ዋነኛው ነው።

“ትችያለሽ እንላታለን፣ ፍቅር እናሳያታለን፣ መጽሐፍት እናነብላታለን፣ እስከ አምስት ዓመቷ ብዙ ነገር አድርገንላታል” የሚሉት ወ/ሮ እህተ “እርሷም አዕምሮዋ ብሩህ ስለነበር ቶሎ ትቀበላለች” ይላሉ።

ዮርዳኖስ በልጅነቷ ብዙም ተግዳሮት ገጥሟት አያውቅም። በተፈጥሮዋ ደስተኛ ናት። ልጆች ይወዷታል። ያ ደግሞ ትምህርቷን ያለምንም ችግር እንድትከታተል አግዟታል። እስከ 10ኛ ክፍል ስትማርም በጣም ጥሩ እንክብካቤ ይደርግላት ነበር።

በትምህርት ቤት ቆይታዋ ዮርዳኖስን ከአንዳንድ መምህራን ጥያቄዎች ቢነሱባትም፣ አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶችም ካለባት እክል አንጻር ላለመቀበል ያቅማሙ የመኖራቸውን ያህል የተቀበሏት እና የደገፏትም በርካቶች ናቸው።

በተለይ ኃይለ ልዑል የተባሉ ርዕሰ መምህር በከባድ ተፈጥሯዊ እክሎች ውስጥ ስለነበረው ስቴቨን ሃውኪንግ ስኬት እየተረኩ ያነቃቋት እና ድጋፍ ያደርጉላት እንደነበር እናቷ ይናገራሉ።

በተጨማሪም አብረዋት የሚማሩ አቻዎቿ እንዲያቀርቧት እና ከጎኗ እንዲሆኑ ይመክራቸው ስለነበረ፣ በትምህርት ቤቷ የነበሩት ተማሪዎች በጣም ያቀርቧት እንደነበር ወ/ሮ እህተ ያስታውሳሉ።

ዮርዳኖስ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ስትዘዋወርም የመግቢያ ፈተና እየተሰጣት እና በብቃት በማለፍ ትምህርቷን እንደቀጠለች እናቷ ይገልጻሉ።

ዮርዳኖስ ከእናቷ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ዮርዳኖስ ከእናቷ ጋር

ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመግቢያ ፈተናን ከወሰደች በኋላ ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገባችው በፍላጎቷ እና በምርጫዋ ነው።

ዮርዳኖስ በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ የሳይኮሎጂ የትምህርት አይነትን የመረጠችው ሰዎችን መርዳት ባላት ፍላጎት እንደሆነ የሚናገሩት እናቷ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስትማር እናቷ ሁሉንም ክፍለ ጊዜ ከጎኗ ተቀምጠው ተምረዋል።

“በዩኒቨርሲቲው የነበረው የአራት ዓመት ቆይታ የአራት ቀን ያክል ነው የሚሰማኝ። በጣም ደስ ብሎኝ ነበር የምንከባከባት። ፈጣሪ እሷን ለእኔ ከሰጠኝ፣ ይህንን ኃላፊነት ደስ ብሎኝ የምወጣበትን ፀጋውን ይሰጠኛል ብዬ ስላመንኩ በዚያ መልኩ ነው የተወጣሁት” ይላሉ ወ/ሮ እህተ።

ዮርዳኖስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ምንም ነገር እንዳልገጠማት የሚጠቅሱት እናቷ በትምህርት ጊዜያት ሁሉ አብረዋት የሚቆዩ ሲሆን፣ በፈተና ወቅት ደግሞ ሌሎች ፈታኞች እየመጡ ፈተናውን ይፈትኗት ነበር።

እናት ከልጃቸው ጋር ክፍል ውስጥ ሲገኙ፣ የዮርዳኖስ ክፍል ተማሪዎች እና መምህራን ለመጀመሪያ ጥቂት ጊዜያት ግር ይሰኙ እንደነበር የሚያስተውሱት ወ/ሮ እህተ፣ “ተማሪዎቹን ስላቀረብኳቸው በጣም ደስ ብሎን እየተመካከርን ነበር ዓመታትን ያሳለፍነው” ይላሉ።

የዮርዳኖስ እናት ወ/ሮ እህተ ብዙ ጊዜያቸውን ከልጃቸው ጋር አሳልፈዋል። በተለይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ አራቱንም ዓመታት አብረዋት ክፍል ውስጥ ተቀምጠው ልጃቸው ትምህርቱን ስትከታተል እርሳቸው ደግሞ ልጃቸውን ተከታትለዋል።

እናም የልጃቸው የጽሑፍ ችሎታ ከሁሉም ተሰጥኦዋ በላይ ጎልቶ ይታያቸዋል። “የምትጽፈውን ነገር ሳነብ እርሷ የጻፈችው መሆኗን እስክጠራጠር ድረስ እገረማለሁ” ይላሉ ወ/ሮ እህተ።

ዮርዳኖስ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በማዕረግ ነው የተመረቀችው። አሁንም ከፍ ባለ ደረጃ ትምህርቷን መቀጠል ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ለሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ሰጥቷታል።

እናቷ እንደሚሉት የወደፊት ፍላጎቷ ሌሎችን መርዳት ነው። “መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥርቼ ሰውን እረዳለሁ” የሚል ዕቅድ አላት።