
ከ 3 ሰአት በፊት
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ባጋጠመ የትራፊክ አደጋ ልጃቸውን አስመርቀው ሲመለሱ የነበሩ አባት ከተመራቂ ልጃቸው ጋር ሕይወታቸው አለፈ።
አቶ ደረጄ ጌታቸው የተባሉት አባት ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀችውን ረድኤት ጌታቸው የተባለችውን ልጃቸው ይዘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ሲመለሱ ነበር የትራፊክ አደጋው አጋጥሞ ሕይወታቸው ያለፈው።
የ51 ዓመቱ የደብረ ሊባኖስ ወረዳ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ደረጄ ሁለተኛ ልጃቸውን አስከትለው በሴት ልጃቸው የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመታደም ወደ ሐዋሳ ያቀኑት ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም. ነበር።
ከምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ቅዳሜ ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም. አባት እና ሁለት ልጆቻቸው ሰሜን ሸዋ ውስጥ ወደ ሚገኛው መኖሪያ ከተማቸው ሻራሮ እየተመለሱ ሳለ ነው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ሱሉልታ ውስጥ የትራፊክ አደጋው የደረሰው።
በአደጋው የአቶ ደረጄ እና የልጃቸው ረድኤት ደረጄ ሕይወት ወዲያው ሲያልፍ የ16 ዓመቱ ታናሽ ልጃቸው ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶበታል።
የአቶ ደረጄ የቅርብ ጓደኛ እና ጎረቤት የሆኑት አቶ አሸናፊ አብዲሳ ለቢቢሲ ሲናገሩ የረድኤት ምርቃትን በማስመልከት ድግስ ተደግሶ ወዳጅ ዘመድ ከቤት ሆኖ መምጣታቸው ሲጠበቅ ነው አደጋው መድረሱ የተሰማው።
“ይህ አደጋ እጅግ ሰቅጣጭ ነው። ለቤተሰብ አይደለም፤ ለጎረቤት አይደለም አደጋውን ለሰማው ሁሉ በጣም ከባድ ነው። ልጃቸውን በደስታ አስመርቀው ወደ ቤት ሲመለሱ፣ ልጅ እና አባት እንደወጡ ቀርተዋል” በማለት አቶ አሸናፊ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።
የሱሉልታ ወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት እንዳለው ለአባት እና ልጅ ህልፈት ምክንያት የሆነው የመኪና አደጋ የደረሰው ሲጓዙበት የነበረው ተሸከርካሪ ከሌላ መኪና ጋር ተጋጭቶ መሆኑን አመልክቷል።
- የኢትዮጵያ የቡና ገበያ የውጭ ንግድ ውጣ ውረዶች25 ሀምሌ 2023
- ልዩ ፍላጎት ላላት ልጃቸው ሲሉ ለዓመታት ዩኒቨርስቲ የቆዩት እናት እና በማዕረግ የተመረቀችው ልጃቸው25 ሀምሌ 2023
- ሩሲያ ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ይላክ የነበረውን እህል መተካት እንደምትችል ፑቲን አስታወቁ25 ሀምሌ 2023
የረድኤት ወላጆች ለመጀመሪያ ልጃቸው ምርቃት ቀድመው ሲዘጋጁ እንደነበረ እኚህ ጎረቤት እና የሟች አቶ ደረጄ ጓደኛ ይናገራሉ።
“ለምረቃው ከብት ታርዶ፣ ጠላ ተጠምቆ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። እኔም እንደ ጓደኛ እና ጎረቤት ተሳትፎ ሳደርግ ነበር። የረድኤት እናትም ተመርቃ የምትመጣዋን ልጃቸውን ለመቀበል እየጠበቁ ነበር። ጎረቤት በሙሉ ቤት ሲደርሱ ለመቀበል እየተጠባበቅን ነው ይህን መርዶ የሰማነው።”
የትራፊክ አደጋው የደረሰው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ሊደርሱ 50 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው፣ ሱሉልታ ወረዳ ቆሬ ሮባ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ነው።
ረድኤት ደረጄ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቷን ተከታትላ ለምረቃ የበቃች ሲሆን፣ ወላጆቿ ከምርቃቷ በኋላ ሥራ ይዛ ትጦረናለች ብለው ተስፋ ሰንቀው እንደነበረ ቢቢሲ ያናገራቸው የሟች ጎረቤት እና ጓደኛ ገልጸዋል።
“አባቷ ‘ልጄ መመረቂያዋ ደርሷል። ተመርቃ ሥራ ከጀመረች ታሳርፈኛለች’ እያለ ይናግረኝ ነበር” ብለዋል አቶ አሸናፊ፣ ከጓደኛቸው ጋር ያደረጉትን ጭውውት በተሰበረ ስሜት በማስታወስ።
በዚህ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው አባት እና ልጅ ትናንት ሰኞ ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም. የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል።
በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የሟቾቹ አቶ ደረጀ ልጅ የረድኤት ወንድም የሆነው የታዳጊ በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገለት መሆኑን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፤ የረድኤት እናት ደግሞ ቀድሞውኑ ታማሚ ስለነበሩ ይህ መሪር ሐዘን ተጨምሮባቸው የጤናቸው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
አደጋው አባት እና ልጆቻቸው ሲጓዙበት የነበረው ሚኒባስ ተሽከርካሪ ከሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ጋር ተጋጭቶ ነው የደረሰው። በዚህም ሳቢያ አባት እና ልጅን ጨምሮ አምስት ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል።
ከሟቾቹ በተጨማሪም የአቶ ደረጄ ልጅ እና የረድኤት ወንድም የሆነው ታዳጊን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ በሌሎች ስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።