ቡና የሚለቅሙ ሴቶች

25 ሀምሌ 2023

የኢትዮጵያ ቡና ላለፉት ጥቂት ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር እያስገባ ነው።

በ2015 በጀት ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቧል።

በዘንድሮው ዓመት ሳዑዲ አረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጅየም፣ ጃፓን እና ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያን ቡና በብዛት የገዙ አገራት ናቸው።

በ2014 ዓ.ም ወደ 300 ሺህ ቶን ቡና ለገበያ ቀርቦ ነበር።

ዘንድሮ 360 ሺህ ቡና ነበር ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የታቀደው። በገቢ ደረጃ ከታየ ደግሞ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት።

ከአምናው አንጻር ዘንድሮ ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና 60 ሺህ ቶን ገደማ የቀነሰ ነው።

ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና መጠኑ ለመቀነሱ የተለያዩ ምክንያቶች ይቀርባሉ።

ዋናው ችግር ተብሎ በኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ የሚገለጸው የዓለም ቡና ዋጋ እና ፍላጎት መቀነስ ነው።

በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግርም ቡና ለገበያ እንዳይቀርብ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከአንዳንድ አካባቢዎች እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ቡና ለገበያ ማቅረብ አልተቻለም ተብሎ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የፀጥታ ችግር በነበረባቸው ጉጂ እና ወለጋ አካባቢዎች “መጀመሪያ ላይ የኤክስፖርት ቡና የቀነሰበት ሁኔታ ነበር። ሆኖም ግን በዚህ ደረጃ ቡና ቀንሷል መባሉ ተጋኗል” ብለዋል።

ለዓለም ገበያ ባለፈው ዓመት 300 ሺህ ቶን፤ ዘንድሮ ደግሞ 240 ሺህ ቶን ቡና መቅረቡን አስታውቀዋል። አገር ውስጥ የተጠጣውን ቡና ከግምት በማስገባት ደግሞ የቡና እጥረት አለመኖሩን አንስተዋል።

አሁንም “ወደ ውጭ የሚላክ ቡና በእጃችን ላይ በበቂ ደረጃ ነው ያለው” ብለዋል።

ከኦሮሚያ በተለይም ከወለጋ የሚመጣው ቡና ቀንሷል መባሉን እንደማይቀበሉት በኦሮሚያ የቡና አብቃዮች ኅብረት ሥራ ማኅበር የንግድ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ምትኩ በቀለም ገልጸዋል።

ኦሮሚያ ውስጥ ቡና ከሚያመርቱ ዞኖች በ12ቱ እንደሚሠሩ ገልጸው በእነዚህ አካባቢዎች “የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን” ጠቁመዋል።

ከሲዳማ ክልል ቡና ወደ ውጭ የሚልኩት እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ በበኩላቸው ከአካባቢያቸው ወደ ውጭ የሚላከው ቡና የተለያዩ ስጋቶች እንደተደቀኑበት ጠቅሰዋል።

የመጀመሪያው የዓለም ቡና ዋጋ መቀነስ ነው። በተለይም ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ዓለም ዙሪያ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በማጋጠሙ ቡና የመግዛት ፍላጎት መቀነሱን ጠቁመዋል።

የዓለም ገበያን ከግምት ያላስገባ እና የብር የመግዛት አቅም ገና ለገና ይቀንሳል በማለት ቡና በሚሰበሰብበት ታኅሣሥ እና ጥር ወራት ቡና ላኪዎች በከፍተኛ ዋጋ መግዛታቸውን ጠቁመዋል።

አገር ውስጥ 6500 ብር ገደማ የተገዛ ቡና በዓለም ገበያ 5500 ብር እንኳን አያስገኝም ይላሉ። ይህንን ነው “ከዓለም ዋጋ ጋር በማይገናኝ እና የማይናበብ በሚመሰል መልኩ በውድ ዋጋ ተገዛ” የሚሉት።

የቡና ዋጋ መቀነሱን የሚስማሙት ዶ/ር አዱኛ “ከአምናው አንጻር ከ30 በመቶ በላይ ነው የዓለም ቡና ዋጋ የወረደው” ብለዋል።

ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በኋላ የዓለም ኢኮኖሚ በመቀዛቀዙ የቡና መግዛት ፍላጎትም በዚያው መጠን መቀነሱን ጠቁመዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም በየጊዜው የዓለም አቀፍ ቡና ዋጋ ለአርሶ ደሮች፣ ለአቅራቢዎች እና ለላኪዎች እንዲያውቁት እየተደረገ ነው። ዓላማው ደግሞ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ በዓለም አቀፉ ዋጋ መሠረት እንዲመራ ለማድርግ ነው።

ሌላኛው ችግር የፍላጎት መቀዛቅ በመሆኑ አዳዲስ ገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋትም እየተሠራ ነው።

“አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን የማፈላለግ፤ በነባር ገበያዎች ውስጥ የመቆየት ዕድሎችን ማስፋት፤ . . . በተለይ ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ ገበያ ለመግባት በስፋት እየተሠራ” ብለዋል ዶ/ር አዱኛ።

የታጠበ ቡና

ባንኮች ብድር ማቅረብ አቁመዋል በሚባል ደረጃ ላይ በመገኘታቸው “ካሽ መክፈል የሚችል የለም” ይላሉ የሲዳማ ቡና ላኪው ሌላውን የዘረፉን ችግር ሲያነሱ።

ቀደም ሲል የሽያጭ ኮንትራት ሳይኖራቸው ጭምር ብድር እንደሚያገኙ የሚገልጹት ላኪው፣ አሁን ግን “ኮንትራት ኖሮም፣ ዶላር አቅርቦም ቢሆን ብድር ማግኘት ከባድ ሆኗል” ብለዋል።

ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ትክክለኛ መረጃ አይደለም የሚሉት ዶ/ር አዱኛ ደግሞ “በቂ ብድር ተሰጥቷቸው ቡና ገዝተዋል” በማለት ያስተባብላሉ።

ላኪዎቹ ቡናውን ለገበያ ያላቀረቡት የዓለም ዋጋን ባላገናዘበ ዋጋ ቡና በመግዛታቸው መሆኑን ጨምረው ጠቁመዋል።

የሲዳማ ቡና ላኪው ሌላም ፈተና እንዳለባቸው ጠቁመዋል – የሎጂስቲክስ እና የስርቆት ችግር። “መንገድ ላይ ምን እንደሚገጥም አይታወቅም ቡና ይሰረቃል፤ [ቡና] በኮንቴነር ተጭኖ ራሱ ጂቡቲ ላይ ሊሰረቅ ይችላል” ይላሉ።

አቅራቢዎች ቡናን በቀጥታ ለላኪዎች የሚያቀርቡበት አሠራር ተዘርግቷል። ይህን አሠራር በመከተል ከሐዋሳ ማዕከል ቡና ደረጃ ይወጣለታል። መሸኛ ተሰጥቶትም ወደ ማዕከል ያመራል።

መረጃው የቡናውን መጠን፣ ደረጃ፣ የመኪናውን የሰሌዳ እና የአሽከርካሪውን ማንነት ይይዛል። ይህንን መረጃ በመጠቀም ቡናው የተለያዩ ኬላዎችን አልፎ አዲስ አበባ ከመድረሱ በፊት የሚያገኘው ትልቁ ኬላ ቱሉ ዲምቱ ያለውን ነው።

ይህንን ኬላ ካለፈ በኋላ ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ቡና መሰረቁን እኚሁ ግለሰብ ለቢቢሲ ገልጸዋል። እሳቸው የታጠቁ የሚሏቸው ‘የመንግሥት አካላት’ “ሌላ ነገር ጭነሃል፤ ትፈለጋለህ በሚል ሾፌሮቹን ይዘው” ቡናው ከነመኪናው ወደ ሌላ ቦታ እንደሚወስዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ መልኩ ጠፋ የተባለ አንድ ተሽከርካሪ ከቀናት በኋላ መገኘቱንም አስታውሰዋል።

ተመሳሳይ ነገር ሁለት የሚያውቋቸው ሰዎች ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል። በአንደኛው አጋጣሚ ዘራፊው እጅ ከፍንጅ መያዙንም ገልጸዋል።

በዝርፊያው ውስጥ በዘርፉ የተሠማሩ ሰዎች እጅ አለበት የሚል ዕምነት አላቸው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት የሚዘረፈው ቡና የምርት ሂደቱ ያላለቀ በመሆኑ፣ ይህንን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ማሽን ማስፈልጉን ነው። ሂደቱ ካለቀ በኋላም የተዘረፈው ቡና ለአገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል ይላሉ።

ቡና የሚለቅም ሰው

ከእንዲህ ካለው ድርጊት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው አለመኖሩን እንዲሁም እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሰዎች ባለመቀጣታቸው “ይህ ወደፊትም ለኤክስፖርት ስጋት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ጨምረውም “ምርት ላይ ችግር የለም። በየመጋዘኑ ቡና ሞልቷል። ገበያ ውድ ስለሆነ ነው የጠፋው። ታች ያለው [ነጋዴ] ፀጥታውን እየፈራ አይጭንም። አሁን ወደ አዲስ አበባ ማምጣትም መጋዘን ላይ ማስቀመጥም ስለሚያስፈራ እርግጠኛ ሳይኮን አምጥቶ ገበያ መፈለግ አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።

ከሁለት ሦስት ወር በፊት እንደዚህ ዓይነት ምልክቶች ይታዩ ነበር የሚሉት ዶ/ር አዱኛ ደግሞ “ይህንን ከፌደራል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጋር በመሆን ወደ ከተማዋ ለሚገባው ቡና ጥበቃ ስለሚደረግ አሁን ምንም ችግር የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ምትኩ ደግሞ ከዝርፊያ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳልገጠማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ይልቅ በፀጥታ ምክንያት የጥራት ችግር እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰዋል። ቡና አንድ በአንድ በጣት መለቀም ቢኖርበትም የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ገበሬዎች በተፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት ቡናውን በፍጥነት በመሸምጠጥ ለመሰብሰብ ይሞክራሉ።

“ቡናው ይደነግጣል። ይህ ደግሞ ጥራት ይቀንሳል። የዘንድሮውን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ዓመትም ጥራት ያለው ቡና እንዳይመረት ያደርጋል። በዚህ ምክንያት እኛ ጋር ሲመጣ ገዢ ያጣል” ብለዋል።

በቡና ጥራት ላይ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ገልጸው፣ ሥልጠና እና የጥራት ፓኬጅ ላይ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ደግሞ የቡና ቅምሻ ማዕከሎችን ወደ ክልሎች ለማውረድ በማሰብ ጂማ እና ሐዋሳ ላይ መቋቋሙን አስታውቀዋል።

ከሲዳማ ክልል ቡናን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ግለሰብ እጃቸው ላይ ያለውን ቡና ለገበያ ቢያቀርቡም “ሌሎች ላኪዎች ግን ምን እንደሚመጣ እየጠበቁ ነው። የአብዛኛው ሰው ቡና መጋዘን ውስጥ ቁጭ ብሎ ነው ያለው” ብለዋል።

መፍትሔው ምን ይሆን ሲባሉ ደግሞ “ላኪው መክሰሩን አውቆ አዕምሮውን አሳምኖ [ለገበያ] ማውጣት ነው። በጣም የሚያሳዝን ወቅት ላይ ነው ያለነው በቡናው ዘርፍ።”

“አንዴ የምጭነው አንድ ኮንቴነር ቡና አስራ ምናምን ሚሊየን ብር ነው። ያ ጠፍቶ ማንም ዞር ብሎ አያየኝም ማለት ነው። ይህ አገር ላይ እምነት እንድታጣ እና ተስፋ ቆርጠህ እንድትወጣ ያደርጋል። መንግሥት ለዚህ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት። ባለሥልጣናት እያወቁ ዝም ነው የሚሉት፣ ምንም የማይመስላቸው በዝተዋል” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከቡና የሚገኘውን ገቢ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲሆን ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

በቂ ምርት ከመኖሩም ባለፈ አዲስ የቡና ምርት ወደ ገበያ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጥራትም ትኩረት ተሰጥቶታል።

“የገበያ መዳረሻዎችን እያሰፋን ስለሆነ የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ መሻሻል ካሳየ፣ የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት መፍትሄ ካገኘ ዕቅዳችን ሊሳካ ይችላል ብለን ተስፋ እንዳርጋለን” ይላሉ ዶ/ር አዱኛ።