በጉራጌ ዞን በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
(አዲስ ማለዳ) በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በምስራቅ መስቃን ወረዳ፤ ሐሙስ ሐምሌ 13/2015 እና ዕሁድ ሐምሌ 16/2015 የታጠቁ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በወረዳው በቼ እና ዲዳ በተባሉ የቀበሌ ከተሞች፤ ምሽት 3 ሰዓት ላይ ጥቃቱ እንደተሰነዘረ እና ግድያዎች እንደተፈጸሙ ምንጮች ከስፍራው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ ከአካባቢው መሰወራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ አካል አለመኖሩ ተጠቅሷል።
በተጠቀሰው ምሽት ላይ ሦሰት ሰዓት አካባቢ በቼ ቀበሌ ውስጥ በተሰነዘረ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው የታወቀ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ዕሁድ ሐምሌ 17/2015 ምሽት ኹለት ሰዓት ገደማ አንድ አባውራ ከነባለቤታቸው እና ጎረቤታቸው ከሆኑ ግለሰብ ጋር መገደላቸውን አዲሰ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
በመስቃንና ማረቆ ብሔረሰብ መካከል ባለው የቆየ አለመግባባት በተደጋጋሚ የሚፈጸም ማንነት ተኮር ጥቃት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ለአካባቢው ማህበረሰብ በነጻነት መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑ ተመላክቷል።
እንደ ነዋሪዎች ገለጻ፤ በአካባቢው ባለው የሰላም እጦት ሳቢያ አብዛኛውየመንግሥት ሠራተኞች ለደኅንነታቸው በመስጋት በሥራ ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ እና ብዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ብሎም የተከፈቱትም አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ተነግሯል።
የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሀመድ ከሐሙስ ሐምሌ 13/2015 እስከ ሐምሌ 17/2015 ድረስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት እንደደረሳቸው ጠቅሰው፤ “በቂ የጸጥታ አካላት ወደቦታው ልከናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም፤ ግድያውን በሚመለከት ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው ወይም አይደለም? የሚለውን ጉዳይ በሚመለከት በመጣራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በጊዜው ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
በዞኑ ኹለቱ ወረዳዎች መካከል ዓመታትን ያስቆጠረው ግጭት ዕልባት ሳያገኝ የቀጠለ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ አካላት ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት ሙከራ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት ከአራት ዓመታት በፊት ሰላም ሚኒስቴር ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ሰፊ ሥራዎችን ይሰራ እንደነበር ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸውን ለማወቅ ተችሏል።