July 25, 2023 – Abebe Bersamo 

ገዢው የብልጽግና አገዛዝ፣ ራሱን ከኢህአዴግ አገዛዝ የተሻለ አድርጎ ሲያቀርብ እየተመለከትነው ነው፡፡ “‘እኔ ብቻ ነኝ ልክ – አይሰራም” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ፣ በህወሃት ጊዜ የዜጎች ሃሳብ በግለሰብ ሃሳብ ይጨፈለቅ ነበር ካለ በኋላ፣ ስለራሱ ሲያወራ ግን ፣ “ብልጽግና ነፃ በሆነ መንገድ በሚንሸራሸር ሃሳብ የራሱን የበሰለ እና ተራማጅ አስተሳሰብ ይዞ አገራችንን ከፍ ለማድረግ የሚተጋ ፓርቲ ነው” ነው ሲል የዜጎችን የመጻፍ፣ የመናገር፣ ህሳባችውን በነጻነት የመግለጽን መብት እንደሚያከብር ለመግልተ ሞክሯል፡፡

የብልጽግና ሰዎች የመግለጫ ጋጋታ ሲያወጡ፣ በዚህ ሊቅ ሲዋሹ፣ ህዝቡን ቢንቁት፣ እንደው የራሳቸው ህሊና ፣ የቅርብ ወዳጆቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸው ምን ይሉናል ብሎ አለማሳባቸው አስገራሚ ነው፡፡

የብልጽግና ገዢዎች፣ የዜጎችን የመናገር፣ የመጻፍ፣ አስተያየት የመስጠት መብት መርገጥ ብቻ አይደለም፣ ዜጎች ሳይጽፉም፣ ሳይናገሩም፣ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ሳይሳተፉም፣ ምንም አይነት ትችት በአገዛዙ ላይ ሳያቀርቡም፣ በማነንታቸው፣ አማራ ስለሆኑ ብቻ በመቶ ሺሆች፣ ከፍርድ ቤት ማዘዣ ሳያመጡ ያፈኑ ፣ አስረው እያሰቃዩ ያሉ አሸባሪዎች ናቸው፡፡

ማሰር ቀላል፣ በማንነታቸው ብቻ ዜጎችን እያፈናቀሉ፣ ቤቶቻቸውን እያፈረሱ፣ ህጋዊ ድሆች አደረግን ብለው የሚደነፉ፣ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳቶችን እየፈጸሙ ያሉ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ እጅግ በጣም ክፉና አረመኔ ገዢዎች የሆኑ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ነው፡፡ ይህ ወንድም በሰፈሩ፣ በመልካም ስራው፣ ችግረኞችን፣ ድሆችን ፣ ደካሞችን በማገዝና በመጠየቅ የሚታወቅ ነው፡፡ በሰፈሩ አንዲት ድሃ፣ የአካል ጉዳተኛ እህት አለች፡፡ እርሷን ለማገዝና ለመርዳት ወደ ቤቷ ይሄዳል፡፡ ከዚች እህት ጋር እያለ፣ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ/ም የኦህዴድ/ብልጽግና ታጣቂዎች መጡ፡፡ በር አላንኳኩም፡፡ እንደ ድርዬ ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ አማርኛ ብዙ መናገር አይችሉም፡፡ስነ ስርዓት ብሎ ነገር የላቸውም፡፡ የፍርድ ቤት ማዘዣ አላሳዩም፡፡ እያመናጨቁ፣ እያዋከቡ፣ በበሸተኛ እህታችን ፊት አፍነው ወሰዱት፡፡ ይህ ወንድም ብርሃኑ ንጉሴ ይባላል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በዚሁ ቀን ነው፣ በአንድ ሰፈር፡፡ ወጣት ነው፡፡ በርበሬ እየነገደ የሚኖር፡፡ ቀኑን ሙሉ በስራ ቦታ ደግሞ፣ ለማረፍ ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ የኦህዴድ/ብልጽግና ታጣቂዎች ወደ ቤቱ ይመጣሉ፡፡ በር አላንኳኩም፡፡ የፍርድ ቤት ማዘዣ አላሳዩም፡፡ ስነስርዓት የላቸውም፡፡ ወጣቱ የሚኖርነትን የቤቱ በር ገንጥለው ገቡ፡፡ ወጣቱን አፍነው፣ እያዋከቡ ወሰዱት፡፡ ይህ ወንድም ሙላት ክፍሌ ይባላል፡፡

ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃሳባችንን የመግለጽ፣ በፖለቲካው የመሳተፍ የዜጎች ሙሉ መብት ነው፡፡ ወንጀል አይደለም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ፣ ብርሃኑ ንጉሴና ሙላት ክፍሌ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል፣ ወይም የሶሻል ሜዲያ አክቲቪስት አልነበሩም፡፡ ጋዜጠኞች አይደሉም፡፡ “ሰባተኛውን ንጉስ” አልተቹም፡፡ ምን ነገር ውስጥ የሉበትም፡፡ ታዲያ የተረኛውና ዘረኛው አገዛዝ አገዛዝ ታጣቂዎች ለምን አሰሯቸው ? በተረኞች ዘንድ እንደ ወንጀለኛ የሚያስቆጥር ነገር በመኖሩ፡፡ አማራ በመሆናቸው፡፡ መታወቂያቸው ላይ “አማ” የሚል በመኖሩ፡፡

ብርሃኑ ንጉሴና ሙላት ክፍሌ ከታሰሩ ሁለት ሳምንት ሊሆን ነው፡፡ የት እንደታሰሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ቤተ ሰብ ፣ ዘመድ አዝማድ በየቦታው ቢያጠያይቅ እነዚህ ወንድሞች የት እንዳሉ ማወቅ አልተቻለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እንግዲህ ያለው ሁኔት ይሄ ነው፡፡ ይህን ጽሁፍ የምታነቡ አገር ቤት ያላችሁ፣ ምንም አይነት ማስተማመኛ እንደሌላችሁ ማወቅ ይኖርባቹሃል፡፡ በናዚ ጀርመን ጊዜ አይሁድ መሆን ወንጀል እንደነበረው፣ አሁን አማራ መባል ወደ ወህኒ የሚያሳሰር ነው፡፡ ይህን አገዛዝ ተባብረን፣ ተረባርበን ማስቆም ካልቻልን፣ እነ ብርሃኑ ንጉሴና ሙላት ክፍሌ የመጨረሻ አይሆኑም፡፡