ዳኒሽ ፓትሪየትስ የተሰኘው ቡድን አባላት

25 ሀምሌ 2023

ኢራቅ ሌሎች በርካታ ሙስሊሞች የሚኖሩባቸው ሃገራት፤ ‘ዳኒሽ ፓትሪየትስ’ የተባለው ቡድን ሰኞ ዕለት ቁርዓን ማቃጠሉን አወገዙ።

ቀኝ ዘመሙ ቡድን ባለፈው አርብም እንዲሁ በተመሳሳይ በፌስቡክ ቀጥታ በተሰራጨ ምስል ኮፐንሃገን ከሚገኘው የኢራቅ ኤምባሲ ፊት ለፊት ቁርዓን አቃጥሏል።

ይህን ተከትሎ አንድ ሺህ ገደማ ሰልፈኞች ባግዳድ ወደ ሚገኘው የዴንማርክ ኤምባሲ አቅንተዋል።

ባለፈው ሳምንት በስቶክሆልም ቁርዓን እንዲቃጠል ዕቅድ መውጣቱን ተከትሎ ባግዳድ የሚገኘው የስዊድን ኤምባሲ የእሣት አደጋ እንደገጠመው ይታወሳል።

የዴንማርክ ቀኝ ዘመሙ ወግ አጥባቂና ፀረ-ኢስላም ቡድን ሰኞ በጠራው ሰልፍ ቅዱስ መፅሑፉን ረግጦ ከኢራቅ ባንዲራ አጠገብ በእሣት አያይዞታል።

የኢራቅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰል ድርጊቶች “ጥላቻና አክራሪነት” እንዲባባስ ይፈቅዳሉ፤ “ማሕበረሰቡ በሰላም አንድ ላይ እንዳይኖርም ያደርጋሉ” ሲል ወቅሷል።

ሙስሊሞች ቁርዓን የፈጣሪ ቃል ነው ብለው ያምናሉ። ሰዎች ሆነ ብለው ይህን ቅዱስ መፅሐፍ ክብር መንሳታቸው እጅግ አስነዋሪ ድርጊት ተደርጎ ይቆጠራል።

በዴንማርክ ከተማ የደረገው ድርጊት በኢራቅ ብቻ ሳይሆን በየመኗ መዲና ሰንዓ ተመሳሳይ ተቃውሞ እንዲነሳ አድርጓል።

ሰልፈኞቹ ዴንማርክና ስዊድን መሰል ድርጊቶች እንዲካሄዱ መፍቀዳቸው አግባብ አይደለም ይላሉ።

በሌላ በኩል ቱርክ ድርጊቱን ቁርዓን ላይ የተቃጣ “የጥላቻ ድርጊት” ስትለው፤ የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ የዴንማርክና የስዊድን አምባሳደሮችን ጠርቶ ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል።

ኢራን በተመሳሳይ ቅዳሜ ዕለት ድርጊቱን በይፋ እንደምትቃወም ገልጣለች።

የኳታር መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት የስዊድን ምርቶች ሱቅ አል ባላዲ ከተሰኘው ትልቁ ገበያ እንዲወገዱ ተደርጓል።

የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በለጠፈው ትዊት “ዴንማርክ ጥቂት ግለሰቦች ቁርዓን ማቃጠላቸውን በእጅጉ ታወግዛለች” ብሏል።

“እኒህ ቀስቃሽና አሳፋሪ ድርጊቶች የዴንማርክ መንግሥት አቋም በፍፁም አይወክሉም። አመፅ መቸም ቢሆን ምላሽ ሊሆን አይገባም።”

ቅዳሜ ዕለት ባግዳድ በተካሄደ ሰልፍ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ዴንማርክ ኤምባሲ ቢያቀኑም የፀጥታ ሰዎች በአስለቃሽ ጭስ ሰልፉን በትነውታል።

በርካታ ኤምባሲዎች ወደ ሚገኙበት የባግዳድ ግሪን ዞን አውራጃ የሚወስደው ድልድይም እንዲዘጋ ሆኗል።

ባለፈው አርብ የስዊድን ኤምባሲ በሰልፈኞች መከበቡን ተከትሎ የኤምባሲው ሠራተኞች ባግዳድን ለቀው እንዲወጡ ሲደረግ ኢራቅ ደግሞ የስዊድኑን አምባሳደር አባራለች።

ይህ የሆነው አንድ ክርስቲያን የኢራቅ ስደተኛ ቁርዓንን እንዲያቃጥል ከስዊድን ፖሊስ ፈቃድ ስለተሰጠው ነው። ግለሰቡ መፅሑፉን ሲረግጥ እንጂ ሲያቃጥል አይታይም።

ፖሊስ የስቶክሆልሙ ድርጊት እንዳይካሄድ ቢከለክልም የሃገሪቱ ፍርድ ቤት የሰዎች የመሰብሰብ መብት መገርሰስ የለበትም ሲል የፖሊስን ዕግድ መሻሩ ይታወሳል።

የስዊድን ባለሥልጣናት ቁርዓን መቃጠሉን ተከትሎ ይህ እስላም ጠል ድርጊት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።