
ከ 5 ሰአት በፊት
በአማራ ክልል፣ ሰሜን ወሎ ዞን፣ ወልዲያ ከተማ ቅዳሜ ምሽት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የከተማዋ ነዋሪ እና ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገለጹ።
ባለፈው ሐምሌ 15/2015 ዓ.ም. ከምሽት ሦስት ሰዓት አንስቶ በታጣቂዎች የተከፈተው ተኩስ ለሰዓታት የቆየ ሲሆን፣ ቢያንስ ለሁለት ሰዎች ሞት እንዲሁም ለሌሎች ሁለት ሰዎች መጎዳት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልዲያ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ቅዳሜ ምሽት በተከፈተው ተኩስ የከተማዋ ነዋሪዎች በእጅጉ ተሸብረው እና ስጋት ገብቷቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ በድንገት ተኩሱን የከፈቱት በተለያየ አቅጣጫ ወደ ከተማዋ የገቡ የታጠቁ ኃይሎች ናቸው።
የከተማዋን ፀጥታ በማደፍረስ አለመረጋጋት ለመፍጠር ያቀዱ ታጣቂዎች ናቸው ተኩሱን የከፈቱት ያሉት አቶ ዱባለ፣ በዚህም ምክንያት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሌሎች ሁለት ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ ደግሞ በተኩሱ አንድ መንግሥታዊ ያልሆ ድርጅት ሠራተኛ፣ አንድ ተማሪ እና አንዲት በመንገድ ላይ ንግድ የተሰማራች ሴት መገደላቸውን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጾ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተመሳሳይ ነገር እንዳጋጠመው አምልክቷል።
- ልጃቸውን አስመርቀው ሲመሰሉ የነበሩ አባት በትራፊክ አደጋ ከነልጃቸው ሕይወታቸው አለፈ25 ሀምሌ 2023
- ልዩ ፍላጎት ላላት ልጃቸው ሲሉ ለዓመታት ዩኒቨርስቲ የቆዩት እናት እና በማዕረግ የተመረቀችው ልጃቸው25 ሀምሌ 2023
- የኢትዮጵያ የቡና ገበያ የውጭ ንግድ ውጣ ውረዶች25 ሀምሌ 2023
ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በማጣራት እንደተረዳው ከቀናት በፊት ወልዲያ ውስጥ ካጋጠመው ክስተት ጋር በተያያዘ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ መገደሉን አረጋግጧል።
ባለፈው ቅዳሜ በወልዲያ ከተማ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ወገን የሌለ ሲሆን፣ የከተማዋ ነዋሪም ለሦስት ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ያሉትን ተኩስ የከፈቱት ኃይሎችን ማንነት ለማወቅ አዳጋች መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባም የጥቃት ፈጻሚዎቹን ማንነት የታወቀ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ይህንን ለመለየት እና ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ማጣራት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከንቲባው ከምሽት ሦስት ሰዓት አስከ እኩለ ሌሊት ስድስት ሰዓት ድረስ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ተኩስ ይሰማ እንደነበር አመልክተው፣ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች የተኩስ ድምጽ የከተማዋን ነዋሪ በከፍተኛ ደረጃ ስጋት ውስጥ አስገብቶት እንደቆየ ነዋሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የወልዲያ ከተማ ነዋሪም ሆኑ ከንቲባው ያረጋገጡት ለሦስት ሰዓታት ያህል በከተማዋ ሲሰማ የቆየው ተኩስ ከአንድ ወገን የሚመጣ እንጂ፣ በሁለት ወገኖች መካከል የሚካሄድ ተኩስ ልውውጥ አልነበረም።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወልዲያ ለሁለት ዓመት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ለወራት መቆየቷ ይታወሳል።
ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ከማደራጀት እና ኢመደበኛ ታጣቂዎችን በተመለከተ የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግሥቱ ካሳለፉት ውሳኔ ጋር በተያያዘ በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች መከሰታቸው ይታወቃል።
በአማራ ክልል ያሉትን ኢመደበኛ የተባሉ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር እና ወደ ሕጋዊ መስመር ለማምጣት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸው ሲነገር ቆይቷል።
ይህ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ሁኔታም ባለፈው ሳምንት በክልሉ ምክር ቤት መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር።
በክልሉ ያለው የመከላከያ እና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ አሳሳቢ ነው ያሉት አንድ የምክር ቤቱ አባልም፣ መስተዳደሩ በክልሉ ካሉ ከታጣቂ ወገኖች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበዋል።