እስር ቤት

ከ 5 ሰአት በፊት

ጋና የሞት ቅጣትን በማስቀረት ቅጣቱን ያስቀሩ በርካታ የአፍሪካ አገራትን ተቀላቀለች።

በአሁኑ ወቅት በጋና 170 ወንድ እና ሴቶች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የቅጣት ቀናቸውን ሲጠባበቁ ነበር። አሁን የእነዚህ ፍርደኞች ቅጣት ወደ የዕድሜ ልክ እስራት ይቀየራል።

በጋና ሕግ ሰውን ለገደለ ተገቢ የሆነው ቅጣት የሞት ፍርድ ነው የሚል ጽኑ አቋም ነበር። ከግድያ በተጨማሪ በአገር ክህደት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ጋናውያን የሞት ፍርድ ሲተላለፍባቸው ነበር።

ምንም እንኳ የጋና ዳኞች የሞት ፍርዶችን ቢበይኑም ለመጨረሻ ጊዜ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ የሆነው እአአ 1993 ነበር።

ከሕዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች ጋናውያን የሞት ቅጣት እንዲቀር ፍላጎት እንዳላቸው አሳይቷል።

ባለፈው ዓመት 7 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ቢሆንም አንዳቸውም ቅጣቱ አልተላለፈባቸውም።

መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ‘ዴዝ ፔናሊቲ ፕሮጄክት (ዲፒፒ)’ የተባለ ተቋም የጋና ፓርላማ ቅጣቱን እንዲያስቀር ከአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ጋር ሲሰራ ቆይቷል።

ዲፒፒ ጋና ከአፍሪካ የሞት ቅጣትን ያስቀረች 29ኛዋ ከዓለም ደግሞ 124ኛዋ አገር መሆኗን ገልጿል።

በቅርብ ዓመታት የሞት ቅጣትን ካስቀሩ የአፍሪካ አገራት መካከል ቤኒን፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፓብሊክ፣ ቻድ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሲዬራ ሊዮን እና ዛምቢያ ተጠቃሽ ናቸው።

የሞት ቅጣቱ እንዲቀር ሲሰሩ የነበሩት የጋና የሕዝብ እንደራሴ አባል ፍራንሲስ-ዣቪዬር ሶሱ “ሞት የተፈረደባቸው እስረኞች ሁሌም ከእንቅልፋቸው የሚነቁት በምድር ላይ የሚያሳልፉት የመጨረሻው ቀናቸው እንደሆነ አድርገው ነው” ብለዋል።

“የሞት ቅጣትን ማስቀረታችን እንደ ማሕብረሰብ ጨካኝ፣ ያልሰለጠንን እና በጨለማ ውስጥ አለመሆናችንን ያሳያል” ብለዋል የሕዝብ እንደራሴ አባሉ ሶሱ።