በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ኮሎኔል ሳዲኦ ካማራ
የምስሉ መግለጫ,በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ኮሎኔል ሳዲኦ ካማራ

ከ 4 ሰአት በፊት

አሜሪካ ከሩሲያው ቅጠረኛ ቡድን ቫግነር ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ሦስት የማሊ ከፍተኛ የጦር መሪዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።

የቅጠረኛ ቡድኑ ተዋጊዎች ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን ከሚዋጋው የማሊ ጦር ጋር በመሆን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥስተ እየፈጸመ ስለመሆኑ ተገልጿል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የቫግነር ተዋጊዎች እአአ 2021 ማብቂያ ላይ በማሊ ከተሰማሩ በኋላ በአገሪቱ የሚገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል።

የማሊ መንግሥት ቅጠረኛ ቡድኑ በአገሪቱ ስለመሰማራቱ ይፋዊ ማረጋገጫ አልሰጠም። ይሁን እንጂ የማሊ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም የሩሲያ ወታደራዊ መኮንኖች ለማሊ ጦር አባላት ስልጠና እየሰጡ ነው ብለው ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ቡድን በማሊ ከ1ሺህ የማያንሱ ወታደሮቹን ስለማሰማራቱ ይታመናል።

ማሊ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጋር አለመግባባቶች ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ፈረንሳይ ወታደሮቿን ከማሊ ማውጣቷን እንደ አጋጣሚ ተጠቅሞ ቫግነር በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ወታደሮቹን ልኳል።

በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ኮሎኔል ሳዲኦ ካማራ፣ የአየር ኃይል አዛዥ ኮሎኔል አሉ ቦይ ዲአራ እና የአየር ኃይሉ ምክትል አዛዥ ሌተናል ኮሌኔል አዳማ ባጋዮኮ ናቸው።

አሜሪካ ሦስቱ ግለሰቦች ቅጠረኛ ቡድኑ በማሊ መሠረቱን እንዲጥል ደግፈዋል የሚል ክስ ታቀርባለች። እነዚህ ከፍተኛ የጦር አመራሮች ተዋጊ ቡድኑ በማሊ እንዲሰማራ በማቀድ እና በማስተባበር፣ በማሊ የማዕድን ማውጫ ስፍራ እንዲያገኝ እንዲሁም ቡድኑ ወደ ጎረቤት አገር ቡርኪና ፋሶ እንዲሰማራ አመቻችተዋል ትላለች።

እንደ አሜሪካ ከሆነ ቡድኑ በማሊ በ2021 ማብቂያ ላይ ከተሰማራ በኋላ የሰላማዊ ሰዎች ሞት በ270 ፐርሰንት ጨምሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ግንቦት ወር ላይ ከቫግነር ትዕዛዝ የሚቀበሉ የማሊ ወታደሮች ባለፈው ዓመት ኅዳር አጋማሽ ላይ በአንዲት መንደር በአምስት ቀናት ውስጥ አብዛኛዎቹ ያልታጠቁ 500 ሰዎችን እንዴት እንደገደሉ ዝርዝር ሪፖርት አውጥቶ ነበር።

የማሊ መንግሥት ይህን ክስ ምንም አይነት ስህተት አልተሰራም ብሎ ካስተባበለ በኋላ በአገሪቱ ተሰማርቶ የሚገኝ 12 ሺህ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲወጣ ጠይቋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች የሆነው ሂዩማን ራይትስ ዎች በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት አሁንም ድረስ በመካከለኛው ማሊ ሰዎች ያለ ፍርድ እየተገደሉ እና በኃይል አድራሻቸው እንዲጠፋ እየተደረጉ ነው ብሏል።

ማሊ ከአስርት ዓመታት በላይ ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችን ስትዋጋ ቆይታለች።