የሩሲያ የመከላከያ ሚንስትር ሰሜን ኮሪያ ሲገቡ

ከ 2 ሰአት በፊት

በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ የሚመራ ቡድን ከቻይና ልዑክ ጋር በመሆን ዛሬ ሰሜን ኮሪያን ይጎበኛል።

የሁለቱ አገራት ልዑካን ሰሜ ኮሪያ የምታከብረውን 70ኛ ዓመት የኮሪያ ጦርነት ፍጻሜ ክብረ በዓል ዝግጅት ላይ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዝግጅቱ በግዙፍ ወታደራዊ ትዕይንት የሚታጀብ ነው።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚል ድንበሯን ከዘጋች በኋላ በሰሜን ኮሪያ ይፋዊ ጉብኝት ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ጉብኝት ሰሜን ኮሪያ ከድንበር መዝጋት ጋር ስላላት ፖሊሲ የሚያሳየው ምልክት ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።

ሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አጋሮቿን ሩሲያ እና ቻይናን ጨምሮ ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ ግንኙነቷን አቋርጣ ቆይታለች። እንደ ምግብ እና መድኃኒት የመሳሰሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን ከውጭ ማስመጣትም አቁማ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ገጥሟት ነበር። የድንበር መዝጋት ፖሊሲዋ እና በኒውክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት የተጣለባት ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ደግሞ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል።

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ዘንድሮ በምታከብረው የድል በዓል ላይ የሩሲያ እና የቻይና ልዑካንን መጋበዟ ምናልባትም በኮሮናቫይረስ ላይ የጣለችውን ቁጥጥር እያላላቸው ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው ተብሏል።

የሁለቱ አገራት ልዑካን የጉብኝት ግብዣ የተደረገው ሰሜን ኮሪያውያን ያለ አፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ሲንቀሳቀሱ በአገሪቱ ሚዲያዎች ከታዩ ከሳምንታት በኋላ ነው።

አሜሪካ ከቫግነር ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው የማሊ ወታደራዊ መሪዎች ላይ ማዕቀብ ጣለችከ 4 ሰአት በፊት

ሩሲያ ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ይላክ የነበረውን እህል መተካት እንደምትችል ፑቲን አስታወቁ25 ሀምሌ 2023

በሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ መሪዎች እንዳይገኙ አሜሪካ እያደናቀፈች ነው ስትል ሞስኮ ወቀሰችከ 5 ሰአት በፊት

በመከላከያ ሚኒስትሩ ሾይጉ የተመራው የሩሲያው ልዑክ ትናንት ፒዮንግያንግ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በቀይ ምንጣፍ ላይ ሲያልፉ ከፍተኛ ወታደራዊ እጀባ የተደረገላቸው ሲሆን “የሩሲያ ፌደሬሽን የመከላከያ ሚኒስትር ጓድ ሰርጌይ ሾይጉ እንኳን ደህና መጡ” የሚል በሩሲያኛ እና በኮሪያኛ የተጻፈ ጽሑፍ ይዘው ተቀብለዋቸዋል።

የቻይናው ልዑክ ደግሞ በቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሊ ሆንግዦንግ ይመራል። ልዑኩ ዛሬ [ረቡዕ] ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ቻይና እና ሩሲያ የሰሜን ኮሪያ የረጅም ጊዜ ወዳጅ ናቸው።

በ1950 (እአአ) ከደቡብ ኮሪያ ጋር በነበረው ጦርነት ቻይና ሰሜን ኮሪያን ለማገዝ ወታደሮችን ልካለች። ከመፍረሷ በፊት ሶቭየት ኅብረትም ተመሳሳይ እገዛ ታደርግ ነበር።

በአሜሪካ የማትወደደው ሞስኮም፣ በአሜሪካ ተመሳሳይ ዕይታ ውስጥ ላለችው ሰሜን ኮሪያ ጥብቅ ወዳጅ ነች።

ምንም እንኳ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ውንጀላውን ውድቅ ቢያደርጉትም፣ ሩሲያ በዩክሬን በምታካሂደው ጦርነት ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የመሳሪያ ድጋፍ እንደምታደርግ አሜሪካ ትከሳለች።

አሁን የጉብኝት ግብዣው የተደረገውም በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል ውጥረቱ ባየለበት ወቅት ነው።

በቤይጂንግ እና ዋሸንግተን መካከል የለው ግንኙነትም በታይዋን ምክንያት እየሻከረ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የአሜሪካ ወታደር ሰሞኑን ወደ ሰሜን ኮሪያ ዘልቆ ገብቶ መጥፋቱን ተከትሎ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ለማናገር ጥረት እያደረገች ነው።

ኪንግ የተባለው የአሜሪካ ወታደር በሥነ ምግባር ችግር ወደ አገሩ ሊመለስ በነበረበት ወቅት ወደ ድንበር አካባቢ ለጉብኝት ተጉዞ በዚያው ሳይመለስ ቀርቷል።

አሜሪካ አባል የሆነችበት የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢው ዕዝ ወታደሩን ለማግኘት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ንግግር መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ነገር ግን ስለዝርዝር ጉዳዩ የተባለ ነገር የለም።