ኤስፔራንስ ኒይራሳፋሪ
የምስሉ መግለጫ,የሩዋንዳ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ኤስፔራንስ ኒይራሳፋሪ

ከ 45 ደቂቃዎች በፊት

የሩዋንዳ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የመጡበት ጎሳ ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ከታደሙ በኋላ ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ይፋዊ የይቅርታ ጥያቄ አቀረቡ።

ኤስፔራንስ ኒይራሳፋሪ የተባሉት የሩዋንዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጎሳቸው ለአባላቱ መሪውን ባስተዋወቀበት ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ፀፀት እና ይቅርታ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንቷ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ካጋሜን ይቅርታ በጠየቁበት ረዥም የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፋቸው ላይ፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በመሳተፍ “አስደንጋጭ ነገር” መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

እንዲህ ባለው የጎሳ ጉዳዮች ውስጥ የገዢው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (አርዩኤፍ) ፓርቲ አባላት እና የመንግሥት ባለሥልጣናት መሳተፍ “የሩዋንዳውያንን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው” በሚል ተቀባይነት የሌለው ነው።

ከኤስፔራንስ ኒይራሳፋሪ በተጨማሪ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተሳተፉ የገዢው ፓርቲ አባላት ይቅርታ ጠይቀዋል።

እንዲሁም በአገሪቱ የአንድ ከተማ ምክትል ከንቲባ የሆኑ ግለሰብም ከሥነ ሥርዓቱ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ሰኞ ምሽት ላይ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ታውቋል።

ባለንበት ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የጎሳ መሪ ትውውቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ የተደረጉት ግለሰብም እራሳቸው ለፕሬዝዳንቱ የይቅርታ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከሦስት አስር ዓመታት በፊት በ100 ቀናት ውስጥ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ 800 ሺህ የሚደርሱ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች ከተገደሉ በኋላ የጎሳ ጉዳይ በሩዋንዳ በከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያዝ ነው።

በየትኛውም ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ዜጎች መካከል ልዩነትን በሚፈጥር ተግባር ውስጥ መሳተፍ በጥብቅ የተከለከለ ሲሆን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደግሞ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ኤስፔራንስ ኒይራሳፋሪ ምንም እንኳን ለፈጸሙት ድርጊት ፕሬዝዳንቱን በይፋ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ ክስተቱ ያላቸውን ሥልጣን እና የፖለቲካ ተጽእኖ ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።

ባለሥልጣኗ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የሥርዓተ ፆታ እንዲሁም የስፖርት እና የባህል ሚኒስትር ሆነው በሩዋንዳ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ ሰርተዋል።

ግለሰቧ በጻፉት የይቅርታ ደብዳቤ ላይ “የጎሳ ስብሰባውን ለማስቆም ምንም ነገር ባለማድረጋቸው” መጸጸታቸውን አመልክተዋል።

በገዢው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ውስጥ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አዲስ ነገር አይደለም።

ተቃዋሚዎች ግን እንዲህ ያሉት የይቅርታ ጥያቄዎች ዓላማቸው በፖሊሲዎች ላይ የተለያ አቋም ያላቸውን ባለሥልጣናት ለማሳፈር እና ተቀባይነታቸውን ለመሸርሸር ነው ይላሉ።