ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ፑቲን
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ፑቲን በመጀመሪያው የአፍሪካ ሩሲያ ስብሰባ ላይ

ከ 1 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ እና ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተናጠል ውይይት እንደሚያደርጉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ረዳት አስታወቁ።

በአፍሪካ አገራት እና በሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚል ከሐሙስ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂም ወደ ሩሲያ ማቅናታቸው ተገልጿል።

በሴንት ቢተርስበርግ ከሚካሄደው ስብሰባ ጋር በተያያዘ ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ የተባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር እንደሚወያዩ የፕሬዝዳንት ፑቲን ረዳት ዩሪ ኡሻኮቭ መግለጻቸውን የሩሲያ ዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተመሳሳይ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው በመጀመሪያው የሩሲያ አፍሪካ ስብሰባ ላይ ተገናኝተው ስለሁለቱ አገራት ታሪካዊ ግንኙነት እና በአህጉሪቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ነበር።

የፕሬዝዳንቱ ረዳት ጨምረውም ፑቲን በጉባኤው ላይ ከሚሳተፉ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር የሚወያዩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ እንደሚገኙባቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ነገ በሚጀመረው የሩሲያ አፍሪካ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሞስኮ ስለማቅናታቸው አስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር እንደሚወያዩ ግን በሩሲያ ባለሥልጣናት ተገልጿል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ መጓዛቸውን በተመለከተ የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፈው ግንቦት ወር በሩሲያ ለአራት ቀናት የቆየ ጉብኝት አድርገው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም ከወራት በፊት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኤርትራ ጉብኝት በማድረግ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተው ነበር።

ከምዕራባውያን ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት የሌላት ኤርትራ፣ ከሩሲያ ጋር በተለያዩ መስኮች ለመተባበር እና አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ ይገኛል።

በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ በተመለከተ ለቀረበባትን ውግዘት በርካታ የአፍሪካ አገራት ባይደግፉትም፣ ኤርትራ ግን ውሳኔውን በመቃወም ብቸኛዋ የአፍሪካ አገር ናት።