
ከ 5 ሰአት በፊት
ሩሲያ ከምዕራባውያን እየደረሰባት ያለውን ጫና ለመቋቋም የአፍሪካ አገራትን ከጎኗ ለማሳለፍ ጥረት ታደርግበታለች የተባለው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ነገ ይጀምራል።
በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በሚካሄደው በሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ 50 የአፍሪካ አገራት ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚሆኑት አገራት በስብሰባው የሚወከሉት በመሪዎቻቸው ነው።
ነገር ግን ምዕራባውያን በተለይም ባላንጣዋ አሜሪካ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በሩሲያ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ ጥረት እያደረገች ነው ሲሉ ከፍተኛ የሩሲያ ባለሥልጣን ክስ ሰንዝረዋል።
የስብሰባው አዘጋጅ ኮሚቴ እስካሁን ድረስ 50 የአፍሪካ ርዕሳነ ብሔሮች በስብሰባው እንደሚገኙ ማረጋገጫ ሰጥተዋል ብሏል።
ከእነዚህ መካከል የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ እና የደቡብ አፍሪካው አቻቸው ሲሪል ራማፎሳ የሚጠቀሱ ናቸው።
በዚህ የሩሲያ-አፍሪካ የምጣኔ ሃብት እና የሰብዓዊ አቅርቦት ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ሁለት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ ላይ ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በግል እየተገናኙ ምክክር ያደርጋሉ ተብሏል።
- ፑቲን በ’ብሪክስ’ ጉባዔ ላይ እንደማይሳተፉ ደቡብ አፍሪካ አስታወቀች19 ሀምሌ 2023
- https://www.bbc.com/amharic/articles/c51qqq57259o20 ሰኔ 2023
- የአፍሪካ አገራት በሩሲያ ወረራ ላይ ለምን ተከፋፈሉ?26 የካቲት 2023
የጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ እአአ 2019 ላይ በሩሲያዋ ሶቺ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ ሁለተኛውን ስብበሳ ደግሞ በአዲስ አበባ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ ነበር።
የስብሰባው ይፋዊ ድረ-ገጽ ስብሰባውን “በሩሲያ-አፍሪካ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ የሚደረግ ሰፊ ኹነት” ሲል ይገልጸዋል።
በመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ እአአ 2019 ላይ ሲካሄድ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው በአፍሪካ ያላትን የንግድ እንቅሰቃሴ በእጥፍ ለማሳደግ ቃል ቢገቡም፣ ሩሲያ በአፍሪካ ያላት የንግድ እንቅስቃሴ ከአምስት ዓመት በፊት በነበረበት ቆሟል።
ከዚህ በተጨማሪም ሩሲያ በአፍሪካ ከምታደርገው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው እንደ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ በመሰሉ በተወሰኑ አገራት ውስጥ ብቻ የተገደበ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ሞስኮ ለአህጉረ አፍሪካ የምታቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ ከዋሽንግተን ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ የውይይት አጀንዳዎች
ቭላድሚር ፑቲን ተሳታፊ በሚሆኑበት የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ከጦር መሳሪያ ንግድ እስከ የእህል ምርት አቅርቦት በአጀንዳነት የተያዙ ጉዳዮች ናቸው።
ባለፈው ሳምንት ሩሲያ ‘ብላክ ሲ’ ከተባለው የዩክሬን የእህል ምርት አቅርቦት ስምምነት መውጣቷን ገልጻ ነበር። በተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪነት የተደረሰው ስምምነት፣ ዩክሬን የእህል ምርቶቿን ከወደቦቿ ወደ ድሃ አገራት ለመላክ አስችሏት ነበር።
ሩሲያ ከዚህ ስምምነት ወጥቻለሁ ካለች በኋላ በነጻ ወይም በጣም ርካሽ በሚባል ዋጋ የአፍሪካ አገራት እህል ማቅረብ የምትችልበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ጠቁማለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሩሲያ ወደዚህ ስምምነት እንድትመለስ ጠይቀዋል።
ከእህል አቅርቦት በተጨማሪ ሌላው የስብሰባው አጀንዳ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እንደሚሆን በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኦሌግ ኦዜሮቭ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የስብሰባው ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ የወጣው መረሃ ግብር እንደሚያሳየው፣ መሪዎች ሁለት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ ላይ በደኅንነት፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ፣ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሁም በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።
የምዕራባውያን ጫና
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞስኮ ከአፍሪካ አገራት ጋር እንዳልመክር ምዕራባውያኑ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለስብሳባ ወደ ሴንት ፒተርስ በርግ እንዳይጓዙ እየወተወቱ ነው በማለት ወቅሳለች።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ትናንት ማክሰኞ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ምዕራባውያኑ የአፍሪካ አገራት በሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ሁሉም የአፍሪካ አገራት ማለት በሚቻል መልኩ በየአገራቱ ባሉት የአሜሪካ እና ፈረንሳይ ኤምባሲዎች የስብሰባው ተሳታፊ እንዳይሆኑ ጫና እየተደረገባቸው ነው ብለዋል።
በተቃራኒው ቻይና እና ሩሲያ በአፍሪካ አህጉር ላይ ያላቸው አድራጊ ፈጣሪነት ያሳሰባት አሜሪካ ባለፈው ዓመት የዩኤስ-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባን በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ማድረጓ ይታወሳል።
ሞስኮ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ አሜሪካ ጫና እየፈጠረች ነው ማለቷን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዋሽንግተን “አፍሪካ ከሌሎች አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት መገደብ አንሻም። የአፍሪካ አገራት አማራጭ እንዲኖራቸው እንፈልጋለን” ብሎ ነበር።
ምዕራባውያኑን እና ሩሲያን የፍጥጫ ውስጥ ያስገባቸው በዩክሬን ላይ የተፈጸመው ወረራን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በተሰጠው ድምጽ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ሩሲያን ከማውገዝ ተቆጥበዋል።
በዚህም ጦርነት ምክንያት ሩሲያ የአፍሪካ አገራትን ከጎኗ ለማሰለፍ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት ወደ አፍሪካ ተደጋጋሚ ጉዞዎች አድርጋለች።
ይህ የሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባም በአህጉሪቱ እና በሞስኮ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የታለመ መሆኑ ግልጽ ነው።