
26 ሀምሌ 2023, 14:34 EAT
ኢኳዶር ውስጥ በእስረኞች ታግተው የነበሩ በርካታ የማረሚያ ቤት ጠባቂዎችን ለማስፈታት መጠነ ሰፊ የጸጥታ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የሃገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ።
ሚኒስትሩ ጁዋን ዛፓታ የጸጥታ ኃይሎች “እስር ቤቶችን ተቆጣጥረዋል” ይበሉ እንጂ የታገቱት በሙሉ ጠባቂዎች ነጻ ስለመውጣታቸው ያሉት ነገር የለም።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀደም ብለው በአገሪቱ በሚገኙ እስር ቤቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶችም እንዲሰማሩ ተደርገዋል።
ጓያስ በተሰኘው ማረሚያ ቤት በተቀናቃኝ ወሮበሎ ቡድኖች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ 11 ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።
በዚህ ማረሚያ ቤት የተፈጠረው ግድያ በሌሎች 12 ማረሚያ ቤቶች ሁከትን ያነሳሳ ሲሆን እስረኞችም የረሃብ አድማ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ቢያንስ በአገሪቱ በሚገኙ አምስት ማረሚያ ቤቶች የእስር ቤት ጠባቂዎች መታገታቸውን የኢኳዶር ማረሚያ ቤት ስናይ ሰኞ እለት አስታውቋል።
ሆኖም ምን ያህል ጠባቂዎች እንደታገቱ ግን ቁጥር ከመስጠት ተቆጥቧል።
የአዙዋይ ግዛት አስተዳዳሪ ኮንሱኤሎ ኦርላና በበኩላቸው ቱሪ በተሰኘው ማረሚያ ቤት ብቻ 53 ጠባቂዎች መታገታቸውን አስረድተዋል።
- በሩሲያ-አፍሪካ ስብሰባ መሪዎች እንዳይገኙ አሜሪካ እያደናቀፈች ነው ስትል ሞስኮ ወቀሰች26 ሀምሌ 2023
- የኦባማ ቤተሰብ ምግብ አብሳይ ተፈሪ በአደጋ አረፈ25 ሀምሌ 2023
- በወልዲያ ባልታወቁ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ26 ሀምሌ 2023
የማረሚያ ቤት አገልግሎቱ ታጋቾቹ ጠባቂዎች በጥሩ ደህንነት ላይ መሆናቸውን ገልጾ ለማስለቀቅም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አስታውቋል።
በጓያስ ማረሚያ ቤት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ማክኞ ዕለት ቀድመው ፍንዳታ መስማታቸውንም ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ዛፓታ ተዘግተው የነበሩ የእስር ቤት በሮችን ለመክፈት ቁጥጥር የተደረገበት ፍንዳታ መፈጸሙን አስታውቀው የአካባቢው ነዋሪዎችን ለማረጋጋት ሞክረዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት 2 ሺህ 700 የጸጥታ ኃይሎች አባላት በጓያስ ማረሚያ ቤት ተሰማርተው “የማረሚያ ቤቱን ሶስት ክንፎች መልሰው ተቆጣጥረዋል” ብለዋል።
በርካታዎቹ የኢኳዶር ማረሚያ ቤቶች ክፉኛ የተጨናነቁ ሲሆን ባለስልጣናቱ የተቀናቃኝ ቡድን አባላትን ለመለየትም ፈተና ገጥሟቸዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ወሮበላ ቡድኖች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ተገድለዋል።