ሞት የተፈረደባት ነጋሴ ከበደ
የምስሉ መግለጫ,ሞት የተፈረደባት ነጋሴ ከበደ

26 ሀምሌ 2023, 18:03 EAT

በኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ በምትገኘው ሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከአራት ወራት በፊት ሁለት ህጻናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለችው የእንጀራ እናት የሞት ፍርድ ተፈረደባት።

ጥፋተኛ ሆና በተገኘችው ግለሰብ ላይ ውሳኔውን ያስተላለፈው የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ሐምሌ 19/ 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ነው።

የቡራዩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ክፍል ባልደረባ የሆኑት እና ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩት ዋና ሳጅን ቀነኒሳ ታደሰ “እርሷን እና መሰሎቿን የሚያስተምር የሞት ቅጣት ውሳኔ ፍርድ ቤቱ በይኖባታል” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነጋሴ ከበደ ብሩ የተባለችው እንጀራ እናት የሁለቱን ህጻናት አንገት ቀልታ በተኙበት ብርድ ልብስ በማልበስ ቤቱ ላይ እሳት ለኩሳባቸው አምልጣለች የተባለው ሚያዝያ 27/2015 ዓ.ም. ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ነበር።

በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት ልጆች አንደኛው የ13 ዓመት ወንድ ሲሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ የ4 ዓመት ተኩል ሴት ናቸው።

ሁለቱም አንገታቸው ተቀልቶ መገደላቸውን ፖሊስ በወቅቱ አሳውቆ ነበር።

ግለሰቧ በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላም ባለቤቷ የነበረውን እና የታዳጊዎቹ አባት የሆነውን አቶ ጌታሁን ባልቻን ለመበቀል ስትል የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሟን እንዳመነች ዋና ሳጅን ቀነኒሳ አስረድተዋል።

ለልጆቻቸው ፍትህ ለማግኘት ሲጠባበቁ የነበሩትን አቶ ጌታሁን ባልቻ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደስ እንደተሰኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“አፈጻጸሙን ለሕግ አካላት እንተወዋለን። ለእኔ እንኳን ባይሆን ለሌሎች ህጻናት እና ለቀሪው ቤተሰብ፣ ይህ የተሰጠው ፍትህ ብርሃን ነው። ብይኑ ለሌሎች ጥሩ ማስተማሪያ ይሆናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን በልጆቻቸው ገድያ ተጠርጥራ ጉዳይዋ ሲታይ በቆየችው ቀድሞ ባለቤታቸው ላይ የተላለፈው የፍርድ ውሳኔ ያላጠበቁት መሆኑን አቶ ጌታሁን በአድናቆት ተናግረዋል።

“ከበፊት ጀምሮ የነበረው የሕግ መላላት እንዳለ ሆኖ በዚህች ሦስት ወራት ውስጥ የፍትህ ሁኔታው መድረሱ ለእኔ ደስ ብሎኛል። ሌሎች ህጻናት እንቅልፍ የሚያገኙበት፣ አሁን ትንሽ እፎይ የሚሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

አክለውም “የእኔ ልጆች እንደ ጧፍ በርተው ለሌሎች ብርሃን መሆን ከቻሉ ተመልሼ የማዝንበት ምንም ምክንያት የለኝም” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆኖም የሞት ፍርድ መፈረዱ ብቻ ሳይሆን አፈጻጸሙ ያላለቀ ከዚህ በፊት ውሳኔዎችንም እየጠቀሱ ጥርጣሬያቸውን ስለሚያነሱ ግለሰቦችም አንስተዋል።

እናም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እና ሕጉን ለሕዝቡ ተዓማኒ እንዲያደርገው አፈጻጸሙ መሆኑንም አጽንኦት በመስጠት አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በሁለት ህጻናት ግድያ አንዲት ግለሰብ የሞት ፍርድ የተፈረደባት ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ከማይደረግባቸው አገሮች አንዷ ናት።

“የውሳኔው ፍጥነት ደስ የሚል ነው። የሚመለከታቸው አካላትም ርብርብ አድርገውበታል” የሚሉት አቶ ጌታሁን፣ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ በቆየው የማኅበራዊ ትስስር በርካቶች ልጆቻቸውን ጎረቤቶች ጋር ጥሎ መሄድ የተለመደ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ ጌታሁን “በአሁኑ ወቅት ግን እንኳን ጎረቤት፣ ከራስ ቤት ልጆችን ጥሎ መሄድ የሚያሳቅቅ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም እንደነዚህ አይነት ወንጀሎች እየተንሰራፉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጌታሁን “ውሳኔው ተግባራዊ ቢሆን ለሌሎች ማስተማሪያ ይሆናል። የሚመለከታቸውን አካላት በተማጽኖ እንለምናለን” ብለዋል።

ሁለት ልጆቻቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ አጥተው ብቻቸውን የቀሩት አቶ ጌታሁን፣ በልጆቻቸው ሞት አስከፊና መራር ሕይወት ውስጥ እንደሆኑም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ልጆች ብዬ የምገልጻቸው አይደሉም። ለእኔ ከምንም በላይ ናቸው። እርቃን እንደ መቅረት ነው የሚቆጠረው። ማንንም ሰው ባለማመን ውስጥ ነው ያለሁት። ሁሉም ነገር የፈጣሪ ፈቃድ ነው ብዬ ነው ራሴን ለማጽናናት የምሞክረው። ግን አስከፊ እና መራር ህይወት ውስጥ ነው ያለሁት፣ ሆኖም ይህቺን ቀን ስጠብቅ ነበር” ብለዋል።

ግድያው የተፈጸመው በሸገር ከተማ ቡራዩ ክፍለ ከተማ ከታ ወረዳ ልዩ ስሙ ሦስተኛ ቡራዩ ጎጥ በሚባል ስፍራ ሲሆን፣ ግለሰቧ ወንጀሉን ከፈጸመች በኋላ ለሦስት ቀናት ያህል ተሰውራ እንደነበር እና በሕዝብ ጥቆማ መያዟን ዋና ሳጅን ቀነኒሳ አስታውሰዋል።

ተጠርጣሪዋን ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ በነበረው ወቅት በሕዝብ ጥቆማ በቡራዩ ክፍለ ከተማ ኤጀርሳ ጎሮ ወረዳ፣ ሳንሱሲ ጫካ ውስጥ ራሷን ለማጥፋት እየሞከረች ባለበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋሏንም ተናግረዋል።

ግለሰበወ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላም መጀመሪያ ላይ አዕምሮውን የሳተ ሰው ታስመስል እንደነበር የሚናገሩት ዋና ሳጅን፣ በማግስቱ ግን ባለቤቷን መግደል ስላልቻለች በልጆቹ ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዷን ማመኗን ያስረዳሉ።

“ናኦል ጌታሁን እና ናቲ ጌታሁን የሚባሉትን ሁለት ህጻናት በተኙበት መጥረቢያ በሚመስል ነገር የተለያየ የሰውነት ክፍላቸውን በመምታት መሞታቸውን ካረጋገጠች በኋላ፣ የራሷን ልብስ ሰብስባ ቤት ውስጥ እሳት ለኩሳ ቤቱን ዘግታ ወጣች። እሳቱ ልጆቹንም አቃጠለ። ከዚያ በኋላ እሷ ጫካ ውስጥ ገብታ ባለችበት ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለችው” ብለዋል።

አቶ ጌታሁን በአካባቢው የሚገኝ ቄራ የሚሰሩ ሲሆኑ፣ ግድያው በተፈፀመበት ዕለት ማምሻውን ከባለቤታቸው ጋር በልጆቻቸው ጉዳይ ተነጋግረው እንደነበር ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“በልጆቼ ጉዳይ ተነጋግረን ነበር። እንደዚህም ምክንያት እንለያይ ተባብለን፤ እርሷም ‘እኔ እሄዳለሁ፣ አንተ እዚህ ትኖራለህ’ አለችኝ” ሲሉ ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገሩትን ያስታውሳሉ።

ምሽት ሲነጋገሩ አቶ ጌታሁን ከባለቤታቸው ዛቻም ሆነ ለእንደዚህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት ያበቃል ብለው የሚጠረጥሩት ጠቋሚ ነገር አለማየታቸውን በወቅቱ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።

አቶ ጌታሁን በ2013 ዓ.ም የልጆቻቸውን እናት በሞት ካጡ በኋላ ባለፈው ታኅሣሥ ነበር ከተጠርጣሪዋ ጋር የተጋቡት።

ሲጋቡም የልጆቻቸውን ሁኔታ ገልፀው፣ ተማምነው እንደነበር ይናገራሉ።

ከእናታቸው ሞት በኋላ ልጆቹ አያታቸው ጋር የነበሩ ሲሆን፣ የአቶ ጌታሁን አባት ባለፈው ነሐሴ ማረፋቸውን ተከትሎ ልጆቹ ወደ አባታቸው ዘንድ መጥተዋል።

ተጠርጣሪዋ ከዚህ በፊት ለአራት ዓመት በአረብ አገር ቆይታ እንደነበር ፖሊስ ቤተሰቦቿን ጠቅሶ ሳጅን ቀነኒ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።

ከዚያ በኋላ እዚያው ቡራዩ አካባቢ “ሽሮ ቤት” ከፍታ ስትሰራ መቆየቷንና ነዋሪነቷም እዚያው ቡራዩ አካባቢ ኤጀርሳ ጎሮ የሚባል አካባቢ እንደሆነ ፖሊስ አክሎ ገልጿል።