

በሕግ አውጭውና በሕግ አስፈጻሚው መካከል ያለው ጉድኝትና መንግሥታዊ ቁመና
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለፓርላማ አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ
July 26, 2023
የሦስቱ የመንግሥት አካላት የፖለቲካ ፍልስፍና ሲነሳ ግልጽ በሆነው የኃላፊነት ልዩነታቸው መሠረት አንዳቸው በሌላኛው ሊተኩ፣ አንዱ የሌላኛውን ሥራ ሊሠራ ወይም ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት አሠራር ሳይሆን፣ አንዱ የሌላውን ሥራ የሚጠይቅበትና እርስ በርስ የሚፈታተሹበት የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አወቃቀር መሠረት መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡
ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ በሚባሉ ስያሜምች በሦስት የሚከፈሉት የመንግሥት አካላት፣ ለእያንዳንዳቸው የተሰጠው በሕግ የተገደበ ሥልጣን የተንሰራፋ የኃላፊነት ክምችት በአንድ አካል ብቻ እንዳይሆን ከማድረጉም በላይ፣ የአገር ሀብትን ተጠያቂነት በሰፈነበት መንገድ ለሚጠበቅበትና ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ አንዱ ሌላውን ጠያቂና ተጠያቂ እንዲሆን የሚያደርግ አሠራር ነው፡፡
የመንግሥት አካላት መለያየት በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሥልጣን አወቃቀርና ክፍፍል በሚያብራራው ምዕራፍ አምስት አንቀጽ 50 ተደንግጓል፡፡ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት መካካል ከፍተኛው የሥልጣን አካል የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን አንቀጹ የሚያብራራ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ተጠሪነቱ ለአገሪቱ ሕዝብ ነው ይላል፡፡
ምክር ቤቱ በማንኛውም ክልል የሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማስቆም ሳይቀር ሲችል በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፈቃድ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ እንደሚቀርብና በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመርያ እንደሚሰጥ ያብራራል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን እንዳለው ሠፍሯል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 እንደተደነገገው ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ናቸው፡፡
በሕግ መንግሥቱ ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣንና ተግባር በሚደነግገው አንቀጽ 74 ንዑስ አንቀጽ 11 ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለአገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግሥት ስለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት ዕቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለአገራዊ ሁኔታ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ቢደነገግም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው ከአባላቱ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡበት መንገድ ሕጉ በሚገልጸው ልክ አለመሆኑ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተካሄዱ የምክር ቤት መደበኛ ስብሰባዎች መስተዋሉ ይገለጻል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምላሽ መስጠት ለማይፈልጉት ጥያቄ፣ ለምክር ቤቱ ክብር በማለት በግላጭ በተደጋጋሚ ያልፉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በሰኔ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመንግሥታቸውን የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ከአባላቱ የተነሱ በተለይም የውጭ ግንኙነት ላይ ያተኮሩ፣ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ተጀምሮ ስለተቋረጠው ስምምነትና የፌዴራል መንግሥታቱ ከሕወሓት ጋር በፕሪቶሪያ ያደረገው ሰምምነት አፈጻጸምና መሰል ጉዳየች ላይ የተነሱ ጥያቄዎችን ያለ ምላሽ ነበር ያለፏቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግል ጥረታቸው ፕሮጀክቶችን የማስገንባት ተግባር ውስጥ በስፋት ሲገቡና ፓርላማው ባለፀደቀው በጀት፣ ዕውቅና ባልሰጠው በመቶ ቢሊዮን ብሮች መገንባት የጀመሩትን የቤተ መንግሥት ግንባታ በተመለከተ ከተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ጥያቄ ሲነሳ፣ በብልፅግና ፓርቲ አባላት በአብላጫ የተያዘው ምክር ቤት አባላት በፌዝ ፈገግታ ሲያሳዩ ተስተውሏል፡፡ ይህ ጉዳይ አንድም ፓርላማው ከአስፈጻሚ ጋር ያለው ግንኙነት አንዱ ሌላውን ተጠያቂ እንዲሆን ከማረጋገጥና (check and balance) ሥርዓት እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ፣ በሁለቱ መካካል ጠንካራ ጉድኝነት መኖሩን የሚያሳይና በርካታ የሕግ ጥሰት ሲፈጸም ፓርላማው የሚያሳየው ዝምታ ለብዙዎች አይዋጥላቸውም፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ማቅረብ ባይችልም፣ ሁለተኛ ዓመቱን አጠናቆ ለክረምት ዕረፍት ለወጣው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2015 ዓ.ም. የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሪፖርት መላኩን በቅርቡ አስታውቆ ነበር፡፡
የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳው የንፁኃን ሞት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የዜጎች ዕገታ፣ ስደት፣ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ እስራት፣ የፀጥታ መደፍረስ፣ ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ የመንቀሳቀስ መብትና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች አደጋ ላይ መውደቃቸውን ኮሚሽኑ ለፓርላማው በላከው ዓመታዊ ሪፖርት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ሰፋ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገልጾ ሪፖርት ቢላክለትም፣ በተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ላይ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው ልክ ዕርምጃ እንዲወሰድበት የሄደበት ርቀት አለመስተዋሉ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ያጭራል፡፡
በሌላ በኩል ፓርላማው በዓመቱ መጨረሻ በሚደረግ መበደበኛ ስብሰባው ላይ ማድመጥ የነበረበትን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሁለተኛውን ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሁነቶች ሪፖርት፣ በጊዜ ማጠር ምክንያት ሳያዳምጥ መቅረቱን የምክር ቤቱ አባላት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ለፓርላማው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ተመሳሳይ የሆኑ የሰብዓዊ የመብት ጥሰቶችን ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ከኮሚቴው አባላት ኮሚሽኑ ሪፖርት ከማውጣት ባለፈ ለተፈጸሙት ጥሰቶች ምን እያደረገ ነው? ከአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ጋር ተናቦ የመሥራት አቅሙ ምን ያህል ነው? በሚል ያቀረቡት ጥያቄ በኮሚሽኑ የሥራ ኃላፈዎች ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ለተነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ ኮሚሽኑ ለሚያወጣቸው መግለጫዎች የማስፈጸሚያ መሣሪያ እንደሌለው ጠቅሰው ዋነኛ መሣሪያው ራሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ የሚቀርበውን ምክረ ሐሳብ አፈጻጸም በሚመለከት አስፈጻሚ አካላትን የት አደረሳችሁ በሚል ምክር ቤቱ እንዲይጠይቃቸው ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ እየለመነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምክር ቤቱ አስፈጻሚ አካላትን አጥብቆ መጠየቅ እንዳለበት አበክረው ተናግረው ነበር፡፡
ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹እንደ አንድ ብሔራዊ ነፃ የሰብዓዊ መብት ተቋም በምክር ቤቱ የተቋቋምነው በነፃነት እንድንሠራ በመሆኑ፣ ከመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ተፅዕኖና አቅጣጫ ነፃ ሆነን መሥራት መቻል አለብን፤›› በማለት መልስ ሰጥተው ነበር፡፡ ‹‹ከመንግሥት ጋር አንድ ዓይነት አቋም ለመያዝ ብለን የምንሠራ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብንም ሆነ ምክር ቤቱን የምናሳዝን ይሆናል፤›› ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ከፓርላማ አባላቱ መሰል የተዛነፉ የሚመስሉ በአዋጅ የተሰጠ ኃላፊነት የሚተላለፍ ጥያቄ የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2015 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ሲያቀርብ፣ ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ኦዲተሯ ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ ፓርላማው በራሱ መከታተልና ማስፈጸም ያለበትን ጥያቄ እንደጠየቃቸው ተናግረው ነበር፡፡ ዋና ኦዲተሯ ባቀረቡት ሪፖርት በበርካታ የኦዲት ግድፈቶችና ክፍተቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡ ይሁን አንጂ የምክር ቤት አባላት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት አጠናቅሮ ከማምጣት ባለፈ፣ የኦዲት ሥራው ተስተካክሎ እንዲወጣ ምን ሠራ የሚል ጥያቄ ለዋና ኦዲተሯ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት ዋና ኦዲተሯ ወ/ሮ መሠረት ፓርላማው የተሰጠውን ኃላፊነት በተገቢው ከመወጣትና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ይልቅ፣ ዋና ኦዲተር የማይመለከተውን ምን አደረገ ተብሎ መጠየቅ ትክክለኛ ጥያቄ አለመሆኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡
ምክር ቤቱ የሚከታተላቸውን ተቋማት የዋና ኦዲተር የሚያቀርበውን የኦዲት ሪፖርት መሠረት፣ አድርጎ መከታተል ካልቻለ ዋና ኦዲተር ተቋማት ላይ ዕርምጃ መውሰድ እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡ አክለው ምክር ቤቱ የራሱን ሚና ቢወጣ ኖሮ ዋና ኦዲተሩን የማይመለከት ጥያቄ ሊጠየቅ አይችልም ነበር ያሉት ወ/ሮ መሠረት፣ ፓርላማው አስፈጻሚውን በራሱ ተከታትሎ አስፈጻሚውን መያዝ ካልቻለ ዋና ኦዲተሩ ምንም ሊያደርግ አይችልም ብለዋል፡፡ የዚህ ዓይነት መሰል የጎራ መደበላለቅን የሚያመላክቱ የአስፈጻሚውንና የሕግ አውጪውን የመሀል መስመር የሚያደበዝዙ ጥያቄዎች መስማት መለመዱ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
ፓርላማው ከአስፈጻሚው አካል ውጪ የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን ሪፖርት የመገምገም ግዴታ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ወቅቱን ጠብቀው መቅረብ የነበረባቸውን የተቋማት አፈጻጸም ዓመታዊ ሪፖርቶች በውሉ ሳይገመገም ዓመቱ አልቆ፣ ምክር ቤቱ ተዘግቶና አባላቱ ለዕረፍት ወደ ተመረጡበት አካባቢ ከሄዱ ሁለት ሳምንት ሆኗቸዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መቅረብ የነበረባቸውና ለሕዝብ ይፋ መደረግ የነበረባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ2015 ዓ.ም. ዓመታዊ ዕቅድ አፈጻጸም ሲያቀርቡ አልታየም፡፡ በእነዚህ ተቋማት ይቀርባሉ ተብለው የሚጠበቁት ሪፖርቶች በአመዛኙ የአስፈጻሚው አካላ ላይ ውግዘት ሊያመጡ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመሆናቸው፣ ሪፖርቱ አለመቅረቡ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ የተያዘ ከመሆኑ የተነሳ የመነጨ ነው የሚሉ አሉ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ የፓርላማ ሥርዓት በሚያራምዱ አገሮች አብዛኛውን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጠው አብላጫ ወንበር ካለው ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲውን በቀላሉ እንዲቆጣጠረውና አባላቱም ለመሪው ታማኝ እንዲሆኑ ዕድል የሚሰጠው ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
በዚህ ዓይነቱ የፓርላማ ሥርዓት በሕዝብ ተመርጦ ምክር ቤት ከገባ አንድ ተመራጭ ይልቅ፣ የወከለው ፓርቲ ትልቅ ሥልጣን እንዳለው በተደጋጋሚ ይታያል፡፡ በአመዛኙ በፕሬዚዳታዊ ሥርዓት ከፓርቲ በላይ የግለሰቦች አቅም የመመረጥ ዕድላቸውን ይወስናል፡፡
በገዥው ፓርቲ በተያዘው ፓርላማ ፓርቲው በተወካዩ ላይ የሚኖረው ጫና ከባድ በመሆኑ ምክር ቤት ውስጥ የገቡ የሕዝብ ተመራጮች ለፓርቲው ከፍተኛ የሆነ የአገልጋይነት ስሜት፣ ተዓማኒነትና ፓርቲው ባሰመረው መስመር እንዲጓዙ ሥርዓቱ የሚያስገድዳቸው መሆኑም ብዙ የተባለበት ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም. የፓርላማ የሥራ ዘመን ከቀረቡ 26 ረቂቅ አዋጆችና አምስት ደንቦች መካከል 20ዎቹን አዋጆችና አንድ ደንብ ማስፀደቁን ያሰታወቀ ሲሆን፣ ፓርላማው ዓመቱ ውጤታማ እንደነበረለት በተለያየ መንገድ ሲገልጽ ነበር፡፡
ሪፖርተር በፓርላማ ሥርዓት በሚተዳደሩ አገሮች ውስጥ በሕግ አውጭው አካልና በሕግ አስፈጻሚው መካከል የሚኖሩ የግንኙነት መርሆዎችን ምን እንደሚመስሉ የጠየቃቸው የቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና አባልና ፖለቲከኛው መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ በዓለም ላይ ሦስት ዓይነት ፓርላማዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያው ጥሩ የሚባሉ ሕጎችን አውጥቶ በሕጉ መሠረት አስፈጻሚውን የሚቆጣጠር፣ ሁለተኛው ደከም ያለ ፓርላማ መሆኑንና ጥሩ የሚባሉ ሕጎችን እንደሚያወጣና ማስፈጸም እንደማይችል፣ ሦስተኛው ሕግ ማውጣትም፣ አስፈጻሚውንም መከታተልና ማስፈጸም የማይችል ዓይነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሦስተኛው ፓርላማ ብዙውን ጊዜ ጩኸት የሚያሰማ (Talking Shop) የሚባል ስያሜ ያለው ነው ብለዋል፡፡
መረራ (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት የኢትዮጵያ ፓርላማ ከሦስቱም በታች ከመሆኑም በላይ፣ ጩኸትን እንኳ በአግባቡ ማሰማት አለመቻሉን ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው የምክር ቤት አባል በነበሩበት ወቅት ይሰማ የነበረውን ያህል ጩኸት እንኳ አሁን እየተሰማ አለመሆኑን ያብራራሉ፡፡ በአስፈጻሚው፣ በሕግ አውጪውና በሕግ ተርጓሚው መካከል ምንም ዓይነት የተጠያቂነትና እርስ በርስ መገማገም አለመኖሩን የሚናገሩት ፖለቲከኛው፣ በዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ የሚነሳው የኃላፊነት ሥራ ክፍፍል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ በፓርላማውና አስፈጻሚው አካል መካካል የሚታው እርስ በርስ የመገማገም ባህሪ ከፓርላማ ሥርዓት የመነጨ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት የመኖር ያለመኖር ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡ ለዚህም የፓርላማ ሥርዓት እናት በምትባለው እንግሊዝ በፓርላማው ውስጥ በማደረግ ፍትጊያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሦስት መሪዎች ከሥልጣን ስለመውረዳቸው ጠቅሰው፣ የፓርላማ ሥርዓት በራሱ ለድክመት ምክንያት አለመሆኑን መረራ (ፕሮፌሰር) ይናገራሉ፡፡
ከምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቧቸው ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ምንጭ የተብራራ መልስ አለማግኘትን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው መረራ (ፕሮፌሰር)፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ቀርቶ ማንም ግለሰብ ማዘዝ ያለበት በራሱ ደመወዝና የግል ሀብት በመሆኑ ሌላው በአገር ስም ሆነ በዕርዳታ ይገኝ፣ የሕዝብ ሀብት በመሆኑ ተጠያቂነት መኖር አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ጉዳይ መሸሽ አይቻልም፤›› የሚሉት ፖለቲከኛው፣ ፓርላማው ይህንን ካልጠየቀ ሌላ ምን ሊጠይቅ ይችላል? ፓርላማነቱስ የቱ ላይ ነው? መጠየቁ ብቻም ሳይሆን እንዴት መጣ? እንዴት ሥራ ላይ ዋለ? ተብሎ በግልጽ መጠየቅና መገምገም አለበት ይላሉ፡፡ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርን የመምራት ኃላፊነት ሲሰጣቸው መብትም ግዴታም አብሮ የተሰጣቸው በመሆኑ፣ በሚሠሩት ሥራ ልክ ተጠያቂነት ከሌለ አገርን እንደ ግል ሀብት ወደ ማስተዳደር ሁኔታ ሊሄዱ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡
የሕዝብ ዋና ዕንባ ጠባቂና የአስተዳደር ምሁሩ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በፓርላማ ሥርዓት የመንግሥት አስፈጻሚ አካልና ሕግ አውጪው የተጣመሩ መሆናቸው የሥርዓቱ መሠረታዊ ድክመት ነው ይላሉ፡፡ በፓርላማ ሥርዓት የአንድ ፓርቲ አባል የሆኑ የሕግ አውጪና ሕግ አስፈጻሚ አካላትን መለየት አስቸጋሪ ስለሚሆንበት አጋጣሚም ያብራራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ምክር ቤት ለአስፈጻሚው የሚያደላ እንደሚመስልም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሕግ አውጪውና ሕግ አስፈጻሚው የተለያዩ ኃላፊነቶች ያሉበት በመሆኑ፣ አንዱ በሌላው ላይ ጣልቃ እንዳይገባና ጠንካራ ምክር ቤት እንዲኖር የምክር ቤቱን አፈ ጉባዔ ከተፎካካሪ ፓርቲ ማድረግ ቢቻል የተሻለ ነው ይላሉ፡፡
ዋና ዕንባ ጠባቂው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት ግልጽነት ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ፓርላማው የማያውቀው አንድም ገንዘብ ሥራ ላይ መዋል የለበትም ብለዋል፡፡ ፓርላማው የማያውቀው በጀት 50 ሳንቲምም ቢሆን ወደ ኢኮኖሚው የሚለቀቅ ከሆነ፣ በኑሮ ውድነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ ትክክለኛ ባለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሸልመውም ሆነ ለምነው ያመጡትን ገንዘብ ፓርላማው ካላወቀው፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሥራ ላይ ሊውል መቻል የለበትም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ሰብዓዊንንትን