ዜና ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ ለሦስት ዓመታት ታስረው የሚገኙ የኦነግ አመራሮች እንዲለቀቁ ተጠየቀ

ዮናስ አማረ

ቀን: July 26, 2023

ፍርድ ቤት በነፃ ቢያሰናብታቸውም ከችሎት ውሳኔ ውጪ ለሦስት ዓመታት ታስረው የሚገኙት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች እንዲለቀቁ ጥያቄ ቀረበ፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ‹‹ሂዩማን ራይትስ ዎች›› ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕግን ለፖለቲካ ትርፍ መሣሪያ የማድረግ ዝንባሌን ሊያስቆሙ ይገባል›› ብሏል፡፡ አብዲ ረጋሳ፣ ዳዊት አብደታ፣ ለሚ ቤኛ፣ ሚካኤል ቦረን፣ ከኔሳ አያናና ገዳ ኦልጀራ የተባሉት የኦነግ አመራሮች፣ እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የታሰሩ መሆናቸውንና አቶ ገዳ ጋቢሳ ደግሞ ከ2021 ጀምሮ በእስር ላይ መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

ታሳሪዎቹ በተያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም፣ በስተመጨረሻ ግን በቀረቡባቸው ፍርድ ቤቶች በነፃ እንዲለቀቁ እንደተወሰነላቸው፣ ይሁን እንጂ ይህን የፍርድ ቤት ውሳኔ በሚፃረር ሁኔታ ታሳሪዎቹ ሳይለቀቁ ቆይተዋል፡፡ ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና የሰብዓዊ መብትን የሚጥስ መሆኑን ያመለከተው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ሰዎቹ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡

ሦስቱ ታሳሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ እንዲፈቱ መወሰኑን፣ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሦስቱ ታሳሪዎች ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያላቀረበባቸው ናቸው፡፡ አንዱ ታሳሪ ግን በዓቃቤ ሕግ አልተከሰሰም፣ ፖሊስ ምርመራ አልከፈተበትም ወይም ፍርድ ቤት አልቀረበም›› በማለት ሰዎቹ በእስር የቆዩበትን ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

ታሳሪዎቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት በየፖሊስ ጣቢያው እየተዘዋወሩ ታስረው መቆየታቸውን አቶ በቴ ገልጸዋል፡፡ ወደ አምስት ፖሊስ ጣቢያዎች የተዘዋወረ ታሳሪ መኖሩንም አመልክተዋል፡፡ ያለ ቤተሰብና ያለ ጠያቂ፣ በቂ ምግብና ሕክምና ሊያገኙ በማይችሉበት በፖሊስ ጣቢያ ለረዥም ጊዜ አመራሮቹ መታሰራቸው፣ እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡