

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ
ዜና አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይን የአስተዳደር ወሰን ወደነበረበት የመመለስ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት ነው…
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይን የአስተዳደር ወሰን ወደነበረበት የመመለስ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥት ነው አሉ
ቀን: July 26, 2023
በሚሊዮን ሙሴ
በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት ‹‹የደቡብና የምዕራብ ትግራይ›› የአስተዳደር ወሰኖችን ተቆጣጥረው የሚገኙ ኃይሎችን አስለቅቆ፣ ለክልሉ የማስረከብ ግዴታና ኃላፊነት ያለበት፣ የፌደራል መንግሥቱ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ በጉብኝት ላይ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በዴንቨር ኮሎራዶ ግዛት ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ የክልሉ የፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ በክልሉ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደርኧ ከለያቸው ቀዳሚ ተግባራት አንዱ የትግራይን ሕዝብ ወደ ቀደመ እንቅስቃሴው መመለስ እንደሆነ ተናግረዋል።
‹‹እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር መጀመርያ ላይ መሥራት አለብን ብለን ካስቀመጥናቸው ነገሮች አንዱ፣ ሕዝባችን ወደ ተለመደው እንቅስቃሴው እንዲመለስ ማድረግ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ የትግራይን ግዛት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ይዞታ መመለስ የግድ ነው፤›› ብለዋል።
የትግራይን የአስተዳደር ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት መመለስ ሲባል፣ መሬት የማስመለስ ጉዳይ ሳይሆን፣ አሁንም ድረስ ስቃይ ላይ የሚገኘውንና የተፈናቀለውን የትግራይ ሕዝብ ወደ ቦታው መመለስና ከገጠመው ችግር ነፃ ማውጣት እንደሆነ አስረድተዋል።
‹‹በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የደቡብና የምዕራብ ትግራይ የአስተዳደር ወሰኖችን ተቆጣጥረው የሚገኙ ኃይሎችን አስለቅቆ ለክልሉ የማስረከብ ግዴታና ኃላፊነት የፌደራል መንግሥቱ ነው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹በአንዳንድ አከባቢዎች በሕገወጥ መንገድ የተመሠረቱ የአማራ ክልል አስተዳደሮች ለማፍረስ፣ ፌደራል መንግሥትና መከላከያ ሠራዊቱ ኃላፊነት ወስደው እየተንቀሳቀሱ ነው፤›› ብለዋል።
አክለውም፣ ‹‹የትግራይ ክልልን የአስተዳደር ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት የመመለሱ ሥራ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ ላይሆን ይችላል፡፡ በእኛ እምነት ግን ይህን ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። በዚህ ረገድ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ አለ፣ ነገር ግን በቂ አይደለም፤›› ብለዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም፣ እስከቻሉት ድረስ አንድም ወጣት ተመልሶ ጦርነት ውስጥ እንዳይገባ ለማድረግ እንደሚሠሩ፣ ይህ ማለት ግን ሁሉም ነገር በእሳቸው ፍላጎት መሠረት ይሄዳል ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ሆኖም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ነገሮች እንዲፈጸሙ እንደሚታገሉና በተቻለ መጠን የሰው መስዋዕትነትን በመቀነስ፣ ከተቻለም ወደ ዜሮ በማውረድ የትግራይን ጥቅም ለማስከበር በኃላፊነት እንደሠሩም አቶ ጌታቸው ለውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
‹‹ትግራይ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ፣ ከሁሉም በላይ ግን ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችን ለማረጋገጥ እንታገላለን፣ ትግሉ መልኩን ሊቀይር ይችላል እንጂ ሊቆም አይችልም፣ አለቆመምም፤›› ሲሉም ተደምጠዋል።
አቶ ጌታቸው በአሁኑ ወቅት ስላለው ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታም ለታዳሚዎቹ አብራርተዋል። ይህ ማብራሪያቸው ማዕከል ያደረገውም ክልሉን በሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደርና (መንግሥት) በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል ያለው ግንኙነት መርህን ሊከተል ይገባል በሚል ነጥብ ላይ ነው።
‹‹በትግራይ ሰላማዊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር ከተፈለገ ፓርቲና መንግሥት መለያየት አለባቸው፣ ይህንን ለማድረግ እየሠራን ነው፤›› ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ የሕወሓት ካድሬ በክልሉ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብቶ ደመወዝ የሚያገኝበት አሠራር መኖሩን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ይህ ሁኔታ ሊቀጥል እንደማይችል ገልጸዋል። ከመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ እየተቆረጠ ለሕወሓት ካድሬ ገቢ እንደሚሰበሰብ፣ በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ የወረዳ አመራሮችም ከሥልጣናቸው ከተነሱ በኋላም ደመወዛቸውና ጥቅማ ጥቅማቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይከፈል እንደነበር የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ይህንን ያልተገባ አሠራር ከደረሰበት በኋላ ቀሪ እንዲሆን በመወሰኑ፣ በርካቶች ቅሬታ እንዳደረባቸው አስረድተዋል።
‹‹ከመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ እየተቆረጠ ለሕወሓት ካድሬ ገቢ የሚሰበሰብ ከሆነ ነገ ባይቶና (የክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲ) ለእኔም ይሰብሰብልኝ ማለቱ ስለማይቀር፣ ይህንን ማስቆም ነበረብን፡፡ በዚህ ሥራችን በርካቶች ቅሬታ ያደረባቸው ቢሆንም ማድረግ ስለነበረብን አድርገነዋል፤›› ብለዋል።