July 26, 2023


አሻድሊ ሐሰን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳደር

ዜና በመተከል ዞን ታጣቂዎች ጫካ የገቡት በመንግሥት የሚሰጠውን የተሃድሶ ሥልጠና ተቃውመው መሆኑ ተነገረ

በመተከል ዞን ታጣቂዎች ጫካ የገቡት በመንግሥት የሚሰጠውን የተሃድሶ ሥልጠና ተቃውመው መሆኑ ተነገረ

ኢዮብ ትኩዬ

ቀን: July 26, 2023

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን የሚገኙ የሰላም ተመላሽ ታጣቂዎች ከእነ ትጥቃቸው ወደ ጫካ የገቡት፣ መንግሥት የሚሰጠውን የተሃድሶ ሥልጠና በመቃወም እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በክልሉ እንደሚንቀሳቀሱና በንፁኃን ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ የሚነገርላቸው ታጣቂዎቹ፣ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረት ሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ ከተማ የተመለሱና በግልገል በለስ ከተማ ከወራት በላይ መቆየታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ሐሙስ ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ከእነ ትጥቃቸው ተመልሰው ወደ ጫካ እንደገቡ ከዞኑ ፖሊስ ለማወቅ ተችሏል።

የሰላም ተመላሾቹ ከእነ ትጥቃቸው ተመልሰው ወደ ጫካ የገቡት የተሃድሶ ሥልጠናውን በመቃወም መሆኑንም ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ፖሊስ  ኮሚሽነር ሀሩን ኡመር ለሪፖርተር አስረድተዋል።

‹‹የተግባባነው ታጣቂዎቹ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና እንዲገቡ ነበር፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹በአጋጣሚ ታጣቃዎቹ በተግባባነው መሠረት በቃላቸው ስላልተገኙ ተመልሰው ወደ ጫካ ገብተዋል፤›› ሲሉ አክለዋል።

ኮሚሽነር ሀሩን በሰጡት ማብራሪያ፣ ተመልሰው ወደ ጫካ የገቡት ሁሉም የሰላም ተመላሾች እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም ወደ ጫካ የገቡት በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ የነበሩት ታጣቂዎች ብቻ እንደሆኑ፣ መንግሥት ባደረገው የሰላም ጥሪ መሠረት በዞኑ ከ2,300 በላይ የሰላም ተመላሾች ከፖሊስ ኮሚሽኑ ጋር እንዳሉ አስረድተዋል።

ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለመፍታት ከተስማሙ በኋላ ለምን ወደ ጫካ እንደተመለሱና ብዛታቸው ስንት እንደሆነ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና እንዲገቡ ሲጠየቁ በመቃወማቸው መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በግልገል በለስ ከተማ የነበሩና ወደ ጫካ ገቡ የተባሉት ታጣቂዎች በአጠቃላይ ከ160 በላይ እንደሆኑ፣ ከእነዚህም መሀል የታጠቁት 106 መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የክልሉ 16ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በክልሉ በአጠቃላይ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ብዛት ከ5,800 በላይ መሆኑን፣ ታጣቂዎቹም የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንደተሰማሩ ተናግረው ነበር።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ብዛት ከ475 ሺሕ በላይ መሆኑን፣ ከእነዚህም መካከል 449,332 ያህሉ ወደ ቀዬአቸው እንደተመለሱ፣ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር የተባሉ ከ10 ሺሕ በላይ ቤቶች፣ ከ100 በላይ ትምህርት ቤቶች መጠገናቸውን ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸው ነበር።

የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ታጣቂዎቹ ተመልሰው ወደ ጫካ በመግባታቸው ሥጋት እንዳለባቸው፣ ከዚህ በፊት የተፈናቀሉና ወደ መኖሪያ ቤታቸው ያልተመለሱ ሰዎች እንዳሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

በግልገል በለስ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ደረሰ በተባለው ጥቃትና ከዚያ በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች ይስተዋሉ በነበሩ ጥቃቶች የተፈናቀሉ ሰዎች በክረምት ወቅት ከመጠለያ ውጪ በመሆናቸው የከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አክለዋል።

የመተከል ዞን ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሀሩን ተፈናቃዮችን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ፣ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑትን መመለስ እንደተቻለ፣ ቀሪዎቹን ደግሞ ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን፣ በየጊዜው ሊጨምርና ሊቀንስ ስለሚችል ወደ መኖሪያ ቤታቸው ያልተመለሱትን ተፈናቃዮች በቁጥር መግለጽ እንደሚያስቸግራቸው አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ ታጣቂዎች አደረሱት የተባለውን የግድያ፣ የማቁሰልና የማፈናቀል ጥቃት በተመለከተ ፖሊስ በአካባቢው በመንቀሳቀስ መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ስላልተገመገመ አሁን የምንሰጠው መረጃ የለንም፣ ሲገመገም መረጃ እንሰጣለን፤›› ብለው የነበረ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን የመርማሪ ኮሚቴ አባላት (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) ውጤቱን ይፋ አለማድረጋቸውን አስረድተዋል። ኮሚሽነር ሀሩን፣ ‹‹ባለፈው የተከሰተውን ክስተት በተመለከተ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ ስለሆነ ምርመራውን ኮሚቴው አጣርቶ ውጤት ሲደርስ እንገልጻለን፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ከተማ የገቡ ታጣቃዎች የኢንቨስተሮች መሬት ላይ እንዲሰፍሩ በመደረጋቸው ኢንቨስተሮች ለሪፖርተር ቅሬታቸውን አቅርበው እንደነበር፣ ችግሩን ለመፍታት ምን እየተሠራ እንደሆነ የተጠየቁት ኮሚሽነር ሀሩን፣ ‹‹መረጃው የለኝም፣ እስካሁን የቀረበ አቤቱታ የለም፤›› ብለዋል።

ኢንቨስተሮች በበኩላቸው የሰላም ተመላሽ ታጣቂዎች በኢንቨስትመንት መሬታቸው ላይ እንዲሠፍሩ እየተደረጉ መሆኑን፣ ይህም ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ከእነ መሣሪያቸው ወደ ጫካ ገቡ የተባሉት ከ160 በላይ ታጣቂዎች እንደገና በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ለማድረግ ምን እየተሠራ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በአገር ሽማግሌዎች በኩል ውይይት ተጀምሯል፣ ይመለሳሉ የሚል እምነት ነው ያለን፤›› ሲሉ አክለዋል።