
አቶ ዓለምአንተ አግደው
ዜና በሕግ አውጪው ዕውቅና ውጪ በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መመርያዎች እንደሚወጡ…
በሕግ አውጪው ዕውቅና ውጪ በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መመርያዎች እንደሚወጡ ታወቀ
ቀን: July 26, 2023
የፌዴራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ቀላል የማይባሉ መሻሻሎች የታዩ ቢሆንም፣ ሕግ አውጪው ዕውቅና ሳይሰጥ በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መመርያዎች እንደሚወጡ ባደረገው ክትትልና በሚቀርቡ አቤቱታዎች ማረጋገጡን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አዋጁ ከሦስት ዓመታት በፊት ፀድቆ በሥራ ላይ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ መሻሻሎች የታዩ መሆናቸውን፣ ይሁንና በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዳለ ባደረገው ክትትል እንደደረሰበት ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
መንግሥታዊ ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው መመርያ የማውጣትና አስተዳደራዊ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን መሠረት፣ መመርያ በሚያወጡበትና አስተዳደራዊ ውሳኔ በሚያስተላልፉበት ጊዜ የዘፈቀደ አሠራር እንዳይኖር አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በሥራ ላይ ቢውልም፣ ሆኖም ከሕግ አውጪው ዕውቅና ሳይሰጥ በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትሉ መመርያዎች እንደሚወጡ በክትትሉ ማረጋገጡን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ከሥልጣን ገደብ በላይ ታልፎ በአስተዳደር ተቋማት የሚሰጡ ውሳኔዎች መኖራቸውን፣ በአዋጁ የተቀመጡ የመመርያ አወጣጥና አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶችና መርሆች አክብሮ ያለመሥራት ክፍተቶች መገኘታቸውን ሪፖርተር የተመለከተውና በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ደኤታው አቶ ዓለምአንተ አግደው ተፈርሞ ለተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ለአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተላከው ደብዳቤ ያስረዳል፡፡
መመርያዎችን በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲወጡ በእናት ሕጉ በተደነገጉባቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜን ጠብቆ አለማውጣት፣ በሥራ ላይ የሚገኙ መመርያዎችን በፍትሕ ሚኒስቴር አስመዝግቦ ለሕዝብ በድረ ገጽ ተደራሽ አለማድረግ ሌላው ሚኒስቴሩ የደረሰበት ችግር እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በመመርያ አወጣጥ ሒደት ሕዝብና ባለድርሻ አካላትን በሕጉ አግባብ አለማሳተፍና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የማዘግየት ችግሮች፣ በአስተዳደር ተቋማት በሰፊው መኖራቸው በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በሥራ ላይ ያሉ መመርያዎችን የአስተዳደር ተቋማት በፍትሕ ሚኒስቴር አስመዝግበው ለሕዝብ ተደራሽ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ የተሰጠ ቢሆንም፣ አሁንም ተመዝግበው ለሕዝብ ተደራሽ ያልሆኑ መመርያዎች እንዳሉ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ከዚህ በኋላ አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ወጥቶ ሥራ ላይ ከዋለበት ከመጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በፊት የነበሩ ነባር መመርያዎችን የማይመዘግብ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
አክሎም ሳይመዘገቡ በሥራ ላይ ያሉ ነባር መመርያዎችን አዋጁ በሚጠይቀው መሠረት ተቋማቱ እንደ አዲስ መመርያ የማውጣት ሒደትን ተከትለው እንዲያወጡ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር በማስመዝገብ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲያደርጉም ፍትሕ ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል በአስገዳጅ ሁኔታ መመርያ እንዲወጣ የሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ፣ በአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጁ አንቀጽ 5 ላይ የተደነገገውን የመመርያ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በመጠበቅ መመርያዎች እንዲወጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴርን ማሳሰቢያ ተከትሎ የፌዴራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ አተገባበር፣ ተቋማት በሕጉ መሠረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ካስታወቁ አንዱ የትምህርት ሚኒስቴር ሲሆን፣ ይህንንም ለ44 የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በላከው ሸኚ ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል፡፡