
ዜና ‹‹በትግራይ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 1,300 ሰዎች በረሃብ ሞተዋል›› የክልሉ አደጋ ሥጋትና…
ቀን: July 26, 2023
- ኮሌራን ጨምሮ ስድስት በሽታዎች ተቀስቅሰዋል ብሏል
- ከመቶ በላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ቢኖሩም ዕርዳታ ማቅረብ አልቻሉም
ከባለፈው ጥር ወር ወዲህ በትግራይ ክልል ከ1,300 በላይ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ ለፌዴራልና ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ባቀረበው ሪፖርት አስታወቀ፡፡ ሪፖርቱ ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የቀረበ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ሳምንታት አያካትትም፡፡
ከምግብና መድኃኒት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚሞቱ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን፣ በአሁኑ ጊዜ 950 ሺሕ ተፈናቃዮች በክልሉ እንዳሉ፣ ከክልሉ ሕዝብ 5.2 ሚሊዮን ያህሉ በዕርዳታ ይኖር እንደነበር ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ከዕርዳታ ስርቆት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች፣ ዕርዳታ በማቋረጣቸው ችግሩ እየከፋ መምጣቱን፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ1,300 አልፏል፡፡ ሐምሌ 15 ቀን ብቻ ከተንቤን ሪፖርት የተደረገልን 56 ሰዎች መሞታቸውን ነው፡፡ ከጥር ጀምሮ ምንም ዕርዳታ የለም፡፡ እስካሁን ሰው ባለው ነገር እየተረዳዳ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ክረምት ነው ምንም የለም፤›› ሲሉ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሪፖርቱ ለዓለም የጤና ድርጅት፣ ለጤና ሚኒስቴርና ለሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ቀርቧል፡፡
በትግራይ 18 የተመድ ኤጀንሲዎች፣ 73 የዓለም አቀፍና የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶችና 53 የአገር ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ምንም ዕርዳታ ማቅረብ አልቻሉም ተብሏል፡፡ ይህም በተለይ የአሜሪካ ኮንግረስን ውሳኔ ተከትሎ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (USAID) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ዕርታዳ በማቋረጣቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡
‹‹ብዙ የዕርዳታ ድርጅቶች እዚህ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ መሬት ላይም ሰዎች እያለቁ መሆኑን እያዩ ነው፡፡ ስንጠይቃቸው ውሳኔው በአገር አቀፍ ደረጃ የተወሰነ ስለሆነ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይነግሩናል፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስ እስካልፈቀደ ድረስ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ይነግሩናል፤›› ሲሉ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ከረዥም ጊዜ በኋላ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ሳምንት 31 ሺሕ ኩንታል ሩዝ፣ ዘይትና የተወሰነ ምግብ ያቀረበ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም እስካሁን እየተበደረም ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ መርዳቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በጣም ጥቂት ተረጂዎችን ብቻ ለመድረስ እንደሚበቃ አክለዋል፡፡
‹‹ችግሩ ከኢትየጵያ መንግሥትና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አቅም በላይ ነው፡፡ ሁሉም የዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶች የተመድ ኤጀንሲዎች በአንዴ ተባብረው ዕርዳታ ካላቀረቡ ሊፈታ አይችልም፡፡፡ ዝም ብሎ ዕርዳታ ማቆም መፍትሔ አይሆንም፡፡ ምርመራ አድርገን ለዕርዳታ የቀረበውን የዘረፉ ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ ምርመራና ተጠያቂነቱ እያሰፈኑ ዕርዳታውን ማቅረብ ይችላሉ›› ሲሉ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በተለይ ከሽሬ አዲግራት፣ መቀሌ፣ አቢ አዲ፣ አክሱም፣ ዓድዋ፣ ራያ፣ አላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨውና ሌሎች አካባቢዎች በተጠራቀሙ ተፈናቃዮች ምክንያት፣ ረሃብና በሽታ እየከፋ መምጣቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው አርሰው መብላት ስላልቻሉ ነው ብለዋል፡፡
ስድስት ተላላፊ በሽታዎች የተከሰቱ መሆናቸውንና ይህም ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኮሌራ፣ ወባ፣ አባ ሰንጋ፣ ውኃ ወለድ በሽታዎችና ሌሎች ጉንፋን መሰል ወረርሽኞች መታየታቸውንና ለሚመለከታቸው ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡