
July 26, 2023

- ትርፉ ካለፈው ዓመት በ25 በመቶ ቀንሷል
– መንግሥት ትርፉን እንዳይወስድበት ጠይቋል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት የሥራ ክንውኑ 20.6 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘ፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 119.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አጠቃላይ ወጪው ደግሞ 98.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በዚህም መሠረት የባንኩ አጠቃላይ ዓመታዊ ትርፍ 20.6 ቢሊዮን ብር ሆኗል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው አጠቃላይ ትርፍ ከዕቅዱም ሆነ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው አንፃር ሲመዘን ቅናሽ የታየበት ነው። ባንኩ በ2014 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት ያገኘው ያልተጣራ ትርፍ 27.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም. ሒሳብ ዓመት ካገኘው 20.6 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ጋር ሲነፃፀር በሰባት ቢሊዮን ብር ወይም በ25 በመቶ ዝቅ ብሏል።
ትርፉ የቀነሰበትን ምክንያትና ተጨማሪ መረጃዎችን ለማጣራት ሪፖርተር የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን ቢጠይቅም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ይሁን እንጂ የባንኩ አጠቃላይ ወጪ መጨመር ለትርፉ መቀነስ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ከባንኩ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የባንኩ አጠቃላይ ወጪ 98.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በሦስት በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል። የባንኩ ወጪ የጨመረውን ያህል ግን ገቢው አልጨመረም። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ያገኘው 119.2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ከዕቅዱ የሰምንት በመቶ ቅናሽ የታየበት ሲሆን፣ ይህ ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1.5 በመቶ ብቻ ብልጫ አለው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 ዓ.ም. ሒሳብ ዓመት የሥራ ክንውኑ የባንኩን አጠቃላይ ሀብት 1.3 ትሪሊዮን ብር ማድረስ ችሏል። ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ የባንክ ኢንዱስትሪ ሀብት ውስጥ 51.7 በመቶ ድርሻ እንዲይዝ አስችሎታል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ 205 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ አቅዶ፣ 163.2 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል። በዚህም የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ሒሳብ መጠን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ 1.1 ትሪሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ18.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።
ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አጠቃላይ ተቀማጭ ሒሳቡን 1.1 ትሪሊዮን ብር በማድረሱም፣ የኢንዱስትሪውን 51.3 በመቶ ድርሻ እንዲይዝና መሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሎታል።
በበጀት ዓመቱ 169 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ለመስጠት አቅዶ 151.2 ቢሊዮን ብር የለቀቀ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከሰጠው ብድር ውስጥ 103 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከዕቅዱ በላይ 141 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉን መረጃው አመልክቷል።
በውጭ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ችሏል። ይህም ከዕቅዱ አንፃር 109.7 በመቶ ያለው አፈጻጻም ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ አንፃርም የ32.1 በመቶ ብልጫ የተመዘገበበት ነው።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ውስጥ 7.8 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በራሱ ያመነጨውን የውጭ ምንዛሪና ልዩነቱን ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሸፈነ መሆኑ ታውቋል። በበጀት ዓመቱ ካቀረበው 7.9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 49 በመቶ የሚሆነው ለነዳጅ ግዥ የተከፈለ ሲሆን፣ 18 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለመንግሥት ግዥዎች (Public Import and Service Payment) መዋሉን ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ከቀረበው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ስምንት በመቶ የሚሆነው ለማዳበሪያ ግዥ የዋለ ሲሆን፣ ለግሉ ዘርፍ የውጭ ግዥዎች የቀረበው የውጭ ምንዛሪ ግን ሰባት በመቶ ብቻ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።
በመቶኛ የተቀመጠው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መረጃ ወደ አኃዝ ሲለወጥም ለነዳጅ ግዥ 3.8 ቢሊዮን ዶላር፣ መንግሥት ለፈጸመው የአገልግሎትና የቁሶች ግዥ 1.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ለማዳበሪያ ግዥ 624 ሚሊዮን ዶላር የዋለ ሲሆን፣ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ግን 546 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር ታውቋል።
በተያያዘ መረጃ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ ትርፉን መንግሥት እንዳይወስድበት መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል። ባንኩ ጥያቄውን ያቀረበው ካፒታሉን ለማሳደግ መሆኑም ታውቋል። ባንኩ አሁን ያለውን የካፒታል መጠን በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ 250 ቢሊዮን ብር፣ በአሥር ዓመት ደግሞ 500 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል።
‹‹መንግሥት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ ትርፍ መውሰዱን እንዲያቆም ጠይቀናል። ምክንያቱም ዓመታዊ ትርፋችንን መልሰን ኢንቨስት በማድረግ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ በጣም እንፈልጋለን፤›› ሲሉ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባለፈው ሳምንት ለሪፖርተር አገረጋግጠዋል።
የአገሪቱ የባንክ ሕግ የባንክ ቆጣቢዎችን ሀብት ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል ባንኮች አጠቃላይ ዕዳቸው እያደገ ሲሄድ በቂ ካፒታል መያዝ እንዳለባቸው እንደሚያስገድድ የተናገሩት አቶ አቤ፣ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
አክለውም የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ለውድድር ከመከፈቱ በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ጉልበቱን ማጠናከር እንደሚያስፈለግው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ያለው ካፒታል የግዴታ ተቀማጭን ጨምሮ 63 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አጠቃለይ የሀብትና ዕዳ መጠኑ ደግሞ 1.3 ትሪሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ መረጃ ያመለክታል። በባንክ ሕጉ መሠረት ባንኮች ለአደጋ ከተጋለጡ የዕዳ መጠናቸው ስምንት በመቶ ዝቅተኛ ካፒታል ሁልጊዜ መያዝ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ ያስገድዳል።