
July 26, 2023

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ለ20ኛ ጊዜ ያዘጋጀው ኮንፈረንስ ታዳሚዎች
በኢትዮጵያ ዋነኛ የኢኮኖሚ ተግዳሮት የሆነው የዋጋ ንረት እንዲባባስ የሚያደርጉ ጉዳዮችን፣ መንግሥት የፖሊሲ መፍትሔ እንዲፈልግላቸው አንድ ጥናት አሳሰበ፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ሐምሌ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዘጋጀው 20ኛው ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ሁለተኛው ቀን ላይ ከቀረቡ የጥናት ውጤቶች አንዱ፣ በምርት አጥናት4ቅራቢዎች በኩል ስለሚባባሰው የዋጋ ንረትን የተመለከተ ነበር፡፡ በዓለም አቀፉ የዕድገት ማዕከል (International Growth Center) ውስጥ በሚገኙ የኢኮኖሚ ተመራማሪዎች የተጠናውና በተለያዩ ጊዜያት የዳበረው ጥናት፣ በአቅራቢዎች በኩል የሚባባሰውን መልከ ብዙ የዋጋ ንረት መንስዔዎች ዳስሶ የፖሊሲ መፍትሔዎች ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
በጥናቱ እንደቀረበው በተለይ በአምራቾች በኩል የዋጋ ንረት እንዲባባስ ቁልፍ ሚና ካላቸው ጉዳዮች ውስጥ በእህል ገበያ ውስጥ ያለው የትርፍ ምጣኔ፣ የምግብ ዋጋ እንዲንር ደላሎች የሚጫወቱት አሉታዊ ሚና የክልል ገበያዎች ከዋና ከተማ ጋር ያላቸው ያልተቀናጀ የገበያ ትስስር እንዲሁም ሌሎች ተጠባቂ ያልሆኑ (ድንገተኛ) ክስተቶች የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን አገሪቱ ባለፉት ዓመታት ከሚታረስ መሬትና ከምርታማነት ጋር በተያያዘ በተለይም በሰብል እህል ምርቶች ዕድገት ብታሳይም፣ ነገር ግን ፈጣን የሆነ የከተማ መስፋፋትና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ማስመዝገቧ ሌላው አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡
ምርታማነት በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ጭማሪ የታየበት ቢሆንም፣ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ምርት (እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የሰብል ምርት) አነስተኛ አቅም ላላቸው አምራቾች ፍጆታ የሚውል መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል፡፡
ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2020 በኢትዮጵያ ከተመረተው የሰብል እህል ብዙኃኑ ለራስ ፍጆታ የዋለ መሆኑንና በሰብል ድርሻ ሲታይ ጤፍ 53 በመቶ፣ ስንዴ 58 በመቶ፣ በቆሎ 74 በመቶ፣ ገብስ 54 በመቶ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ተብሏል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ ካመረተው ምርት ለገበያ የሚያቀርበው ከአንድ ሦስተኛ ድርሻ በታች መሆኑን አመላካች መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
በዓለም አቀፍ የዕድገት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ስንሻው ታምሩ (ዶ/ር)፣ የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ዋነኛ የኢኮኖሚ ችግር መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሦስት እስከ አራት በሚደርሱ ወቅቶች በከፍተኛ የዋጋ ንረት ሒደቶች ውስጥ እንዳለፈች ገልጸው የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ2002/03 በተከሰተው ድርቅ፣ በ2008/11 በዓለም አቀፍ ደረጃ በምግብ ዋጋ መናር የተነሳ የአገር ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት ማሻቀብ ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. በ2018 ከፍተኛ አኃዝ ያሳየውና እስከ 40 በመቶ የደረሰ የዋጋ ንረት መመዝገቡ በጥናቱ የተዳሰሰ ሲሆን፣ በተለይም የኮቪድ ወረርሽኝና በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ምን ያህል ተፅዕኖ ማሳደራቸውን በተመለከተ ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም እያጠናው መሆኑን ስንሻው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አሠርት ዓመታት ተደናቂ የሆነ የሰብልና የእህል ምርት ዕድገት ያስመዘገበች መሆኑንና በተለይም ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ ያለፈው አሥር ዓመት ዕድገታቸው ከሦስት እጥፍ በላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ ምንም ያህል አማላይ የሚባል ዕድገት ቢሆንም በዚያው ልክ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ቁጥር መመዝገቡን፣ ለአብነትም እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2022 ባለው ጊዜ 64 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ከ75 ሚሊዮን ወደ 123 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን ገልጸዋል፡፡
በገጠርም ሆነ በከተማ ያለው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ፈጣን የሆነውን የከተማ መስፋፋት ተከትሎ፣ በተለይም በከተማ የሚኖሩ ዜጎች የራሳቸውን ምግብ የማያመርቱና በገጠር አምራቹ ላይ እንደሚንጠለጠሉ ተገልጾ፣ ገበሬውም ራሱን በምግብ ዋስትና ከመቻል አልፎ እያደገ ለመጣው የከተማ ሕዝብ ፍጆታ ምርት እንዲያቀርብ እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል፡፡
አምራች ገበሬዎች ከሚያመርቱት ብዙኃኑን ለራሳቸው ፍጆታ እንደሚያውሉ፣ ለገበያ የሚያቀርቡትም አነስተኛ መጠን ያለው እንደሆነ፣ ምርት ቢጨምርም ትርፍ ምርት ባለመኖሩ የገበያ ፍላጎትና አቅርቦት ያልተጣጣሙበት ስለመሆኑ በጥናቱ የተለየ አንገብጋቢ ጉዳይ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በግብይቱ መሀል ያለው ጣልቃ ገብ (ደላላ) የምግብ ዋጋ ንረት ከፍተኛ እንዲሆን አሉታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው የተባለ ሲሆን፣ በገጠር አምራቹ አካባቢና በከተማ በሚገኙ አከፋፋዮች (ቸርቻሪዎች) አካባቢ በርካታ ደላሎች እንዳሉ፣ ይህም ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ስለመሆኑ በብዛት ሲገለጽ እንደማይስተዋል ስንሻው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በገበያው ውስጥ ባሉ ደላሎች ምክንያት ገበሬው በምርቱ ላይ የመወሰንና የመደራደር ዕድሉ የመነመነ እንደሆነ፣ ይህም በዋጋ ንረት ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ በሰብልም ሆነ በአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ትስስር እንደሚንፀባረቅ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የገበያ ቦታዎች ቅንጅት እየጨመረ ካለው የዋጋ ንረት ጋር ያላቸውን አስተዋጽኦ የተመለከተው ጥናቱ፣ በተለይም የክልል የገበያ ሥፍራዎች በአዲስ አበባ ከሚገኙት የምርት መሸጫ ማዕከላት ጋር ያላቸው ትስስር ሲታይ እ.ኤ.አ. በ2015 ጠንካራ የሚባል ምርትን የመለዋወጥ ቅንጅት እንደነበረ፣ ነገር ግን ከዚያ በኋላ የክልልና የአዲስ አበባ ገበያ ልውውጥ ማሽቆልቆል የተስተዋለበት ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በአገሪቱ የነበሩት የተለያዩ ክስተቶች የገበያ ትስስሩን እንዳዳከሙት፣ እነዚህም ሰላማዊ ሠልፎችን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የተስተዋሉት የትጥቅ ግጭቶች፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ የኃይል ዕርምጃዎች፣ ባጠቃላይ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በእህል ምርት አቅርቦት ላይ የጎላ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡
ጥናቱ እንዳመለከተው፣ የተለያዩ አባባሽ ፖለቲካዊ ክስተቶች መፈጠራቸው በኢትዮያ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በተለይም የእህል ምርት በሆኑት ጤፍና ስንዴ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተዋጽኦ እንዳላቸውና የዋጋ ንረቱን እንዳባባሱ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡
ስንሻው (ዶ/ር) ባቀረቡት የጥናት ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት፣ ለገበያ የሚቀርብ ትርፍ ምርት ባለበት የቆመ ስለሆነ መንግሥት ለአጭር ጊዜ የምግብ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት መቀጠል አለበት፡፡
በሌላ በኩል በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የመፍትሔ አመለካቾች ወይም ሊታሰብባቸው ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ በተለይም አነስተኛ የሚባሉትን አርሶ አደሮች ምርታማነት ማሳደግና የገበያ አድማሳቸውን ማስፋት ነው ተብሏል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ደላሎችን በተመለከተ ተጨማሪ የምርመራ ጥናቶች ሊደረጉ እንደሚገባ ተብራርቷል፡፡
የዋጋ ንረት እንዲባባስ መንስዔ የሚሆኑ በተለይ ለፖለቲካዊ ክስተቶች መንግሥት መፍትሔ ሊያበጅ ይገባል ተብሏል፡፡ በተለይም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማብረድ፣ መንግሥት ጉልህ ሚና ሊጫወት እንደሚገባው ስንሻው (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡