ዜና
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ፕሬዝዳንት ፑቲን የአቶሚክ ኢነርጂ ትብብር ፍኖተ ካርታ እንደሚፈራረሙ ገለጹ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: July 26, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ና የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአቶሚክ ኢነርጂን ጠቅም ላይ ለማዋል የትብብር ፍኖተ ካርታ እንደሚፈራረሙ አስታወቁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን: በሁለተኛው የአፍሪካ ራሺያ የጋር ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ በራሺያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የገባ ሲሆን፣ ልዑካን ቡድኑ ከራሺያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በመገናኘት፣ በሁለቱ አገራት ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ መክሯል።

ነገ ከሚጀመረው የራሺያ አፍሪካ የጋራ ጉባኤ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያና ራሺያ 15 የሚደርሱ የሁለትዮሽ የትብብር ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)ገልጸውላቸዋል።

የትብብር ስምምነት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ፣ ኢትዮጵያ ከአቶሚክ ኃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨትና ለመጠቀም የሚያስችላት የትብብር ፍኖተ ካርታ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ፑቲን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ አገራት በሳይበር ደህንነትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ ለመተባበር ስምምነት እንደሚፈራረሙ ታውቋል።

“በራሺያ ቆይታዎ ወቅት የትብብር ስምምነት የምናደርግባቸውን የሰነዶች ፓኬጅ አዘጋጅተናል፤ ከነዚህም መካከል የመረጃ ደህንነት ስምምነት ፣ በአየር ትራፊክ ፣ በኢንፎርሜሽንና የግንኙነት ቴክኖሎጂዎች መስክ የመግባቢያ ሰነድ ፣ የአቶሚክ ኢነርጂን ለመጠቀም የሚያስችል የትብብር ፍኖተ ካርታ ፣ በጉምሩክ አገልግሎቶች ፕሮቶኮልና ሌሎች” ሲሉ ፕሬዚደንት ፑቲን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተናግርዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበኩላቸው ከኢትዮጵያና ራሺያ የሁለትዮሽ ትብብር በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል።