ኪም ሚሳኤሎችን እያሳዩ

ከ 2 ሰአት በፊት

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን አገሪቷ ያላትን አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች ለሩስያ የመከላከያ አዛዥ ሰርጌይ ሾይጉ አሳዩ።

ኪም ጆንግ ኡን በሰርጌይ ሾይጉ የሚመራ የሩሲያ ልዑካን እና አንዲሁም የቻይና ባለስልናጣትን ጋብዘዋል።

የሩሲያና የቻይና ባለስልጣናት በመዲናዋ ፒዮንግያንግ የተገኙት የኮሪያ ጦርነት መቋጫ የሆነውን 70ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ለመገኘት ነው።

በዛሬው ዕለት ሐምሌ 20/ 2015 ዓ.ም የሚከበረው በዓልም ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ትዕይንት የሚታይበት ነው።

መሪው ለሩሲያው መከላከያ ኃላፊ ካሳይዋቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል አህጉራትን ተሻግረው መወንጨፍ ይችላሉ የተባሉት ህዋሶንግ ባሊስቲክ ሚሳኤይል አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል።

ይህ ሚሳኤል በሚያዝያ ወር ሙከራ ተደርጎበት የተሳካ ውጤት ተገኝቶበታል ተብሏል።

በተጨማሪም ሁለት አዳዲስ ዲዛይን ያላቸው የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ለእይታ መቅረባቸውም ተዘግቧል።

ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ላይ መፈጸሟን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ታቀርባለች የሚል ተደጋጋሚ ክስ መቅረቡ ይታወሳል።

ሆኖም አገራቱ ይህንን ክስ አይቀበሉትም።

የሰሜን ኮሪያ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሩስያው መከላከያ ሚኒስትርና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች በመከላከያ ዙሪያ እና በዓለም አቀፍ የጸጥታ ሁኔታን ጨምሮ “በጋራ ጉዳዮች” ላይ ተወያይተዋል ሲልም ዘግቧል።

የኮሪያን ጦርነት በዘላቂነት የቋጨው ስምምነት የሰሜን ኮሪያ የድል ቀን ሐሙስ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም በከፍተኛ የወታደራዊ ትዕይንት የሚጠናቀቀቅ ሲሆን የልዑካኑ ጉብኝትም በዚሁ እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል።

ሁለቱም አገራት ሩሲያ እና ቻይና የሰሜን ኮሪያ የረጅም ጊዜ አጋር ናቸው።

ኮቪድ-19 ከተቀሰቀሰ በኋላ በራቸውን ጥርቅም አድርገው የነበሩት የሰሜን ኮሪያው መሪ የውጭ አገራት መሪዎች ሲጎበኟቸውም የመጀመሪያው ነው።

ኪም ለመጨረሻ ጊዜ የውጭ አገራት መንግሥት ተወካዮችን ለወታደራዊ ትዕይንት የጋበዙት በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር።