የትግራይ ኃይል መቀለን በተቆጣጠረበት ወቅት

ከ 3 ሰአት በፊት

በፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት መሠረት ከ50 ሺህ የሚበልጡ የትግራይ ኃይል አባላት ከሠራዊቱ መሰናበታቸውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።

በዚህም የሠራዊቱ አባላት በክብር ወደ የቤታቸው ሽኝት እንደተደረገላቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት እና የሰላም እና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ረቡዕ ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም. መናገራቸውን የትግራይ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የሠራዊቱ አባላትን አሰናብቶ ከሕብረተሰቡ ጋር የማዋሃድ እና መልሶ የማቋቋም ተግባር መሠራት የነበረበት ከፌደራሉ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር ቢሆንም፣ አንዳንድ መጓተቶች መታየታቸውን ጄነራሉ አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ሥራ መጀመር ከነበረበት እንደዘገየ የገለጹት ጄነራሉ ለሰላሙ ዘላቂነት ሲባል የመጀመሪያው ዙር ስንብት መጀመሩንም መግለጻቸው ተዘግቧል።

“ዛሬ ከሁሉም ክፍለ ሠራዊት የተውጣጡ ከ50 ሺህ በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በክብር የመሸኘት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል። መሆን የነበረበት ከፌደራል መንግሥቱ የተሃድሶ ኮሚሽን የማቋቋሚያ ክፍያዎች ይዘው ቢሆንም ሰላሙን እና ልማቱ በተፋጠነ መልኩ እንዲሄድ የሚታዩ መጓተቶችን ሳንጠብቅ መጀመር ስላለብን ጀምረናል” ብለዋል።

በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተው በዘላቂነት ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይ ከዚህ ቀደም ተገልጿል።

የመልሶ ማቋቋም ግንባታው በትግራይ፣ አማራ እና አፋርን ጨምሮ የቀድሞ ተዋጊዎችን በማሰናበት ከሕብረተሰቡ ጋር ለማቀላቀል የሚያስፈልገው እጅግ ከፍተኛ ወጪ ችግር መሆኑንም ኮሚሽኑን የሚመሩት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መናገራቸውም ተዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት ለተሰናበቱት የትግራይ ኃይሎች ለወራት መቆያ የሚሆን ገንዘብ የተሰጣቸው ሲሆን ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽኑ ዘላቂ የማቋቋሚያ ፕሮግራም የሚያዘጋጅላቸው ከሆነ ጥሩ አማራጭ መሆኑን ጄነራል ታደሰ ጠቅሰዋል።

ሆኖም ከትግራይ በኩል ዘላቂ የሆነ የማቋቋሚያ ፕሮግራም እየተዘጋጀ ስለመሆኑም በዚሁ አጋጣሚ አስረድተዋል።

“እነዚህ ለትግራይ ሕዝብ ህልውና ዋጋ የከፈሉ ናቸው። እነሱን የማቋቋም ጉዳይ የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት ኃላፊነት እና ግዴታ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የትግራይ ሠራዊት ጦር ጉዳተኞች እንዲቆዩ በተደረጉበት ማዕከል ውስጥ አስፈላጊውን የሕክምና ድጋፍ እንዲሁም በቂ ምግብ እና አልባሳት ስለማይቀርብላቸው በችግር ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ የአደባባይ ተቃውሞ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሰልፈኞቹን ለማስቆም አስለቃሸ ጋዝ መጠቀማቸውም መዘገቡ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ጄነራሉ ሌላኛው ያነሱት ጉዳይ በፕሪቶሪያው ግጭትን የማቆም ዘላቂ ስምምነትና በናይሮቢው የትግበራ ሰነድ መሰረት “የፌደራሉ መንግሥት ወደ ትግራይ መመለስ የነበረባቸውን ቦታዎች እስካሁን ባለመመለሱ በአካባባቢው የፀጥታ እና የደኅንንት ስጋት ተፈጥሯል” ብለዋል።

በእነዚህ አካባቢዎችም የትግራይ ሠራዊት እንዲቆይ “መገደዱንም ነው” የተናገሩት።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና የናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ መፍታት የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ሆኖም በክልሉ ያሉት የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸው እና በክልሉ በሚፈጸሙ ጥሰቶችም ስማቸው ሲጠቀስ ይሰማል።

የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተፈጻሚነት የሚከታተለው የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ ማስረከባቸውን እንዲሁም ትጥቅ መፍታታቸው ሂደት በጥሩ መልክ መከናወኑን ከዚህ ቀደም አስታውቋል።

ሆኖም ኮሚቴው በምዕራብ እና በደቡብ ትግራይ እንዲሁም በኤርትራ ቁጥጥር ስር ባሉ ሰሜናዊ የትግራይ አካባቢዎች ስፍራዎች እንዳይደርስ መከልከሉም ተገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ የባለሙያዎች ቡድን ስለ ትጥቅ መፍታቱ ሂደት መግለጫዎችን ቢሰጥም ሌሎች ተፈጸሚ መሆን ስለሚገባቸው ጉዳዮች እና ጥሰቶችን በይፋ ሪፖርት የሚያደርግበት ሥልጣን አለመኖሩ አንድ ክፍተት መሆኑንም የሰላም ሂደቱን የገመገመው ‘አፍሪካንስ ፎር ዘ ሆርን’ የተሰኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ጥምረት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን የቀጠፈውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከዘጠኝ ወራት በፊት መደረሱ ይታወቃል።

የሰላም ስምምነት መሠረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሠረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።

ከተሰናባቾቹ መካከል በከፊል
የምስሉ መግለጫ,ከተሰናባቾቹ መካከል በከፊል

ከሠራዊቱ የተሰናበቱ የትግራይ ኃይል አባላት ምን ይላሉ?

በሽረ በተካሄደው የስንብት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ከተሰናባች ሠራዊት አባላት መካከል የተወሰኑትን አነጋግሯል።

አስተማማኝ ሰላም እንፈልጋለን

የትግራይን ሠራዊት በጥቅምር ወር 2014 የተቀላቀለችው ሮዛ ኃይለ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በሽራሮ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች።

ጦርነቱ መከሰቱን ተከትሎ ትምህርቷን ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን ከቤቷም ለመፈናቀል ተገደደች።

ሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ውስጥ ካሉ በርካታ ተፈናቃዮች ጋር ኑሮን ብትጀምርም ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ ሠራዊቱን ለመቀላቀል እንደወሰነች ትናገራለች።

በትግራይ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተበትም ወቅት በነበሩ ውጊያዎች ተሳትፋለች።

በአሁኑ ወቅት ተሰናባች ከሆኑ የሠራዊቱ አባል አንዷ የሆነችው ሮዛ “በክብር በመሰናበትዋ ደስተኛ” መሆኗን ገልጻ፣ “ነገር ግን ዘላቂ ሰላም፣ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን” ብላለች።

ሰላም ከሆነ ወደ ትውልድ ስፍራዋ ሽራሮ ተመልሳም መኖር እንደምትፈልግ ተናግራለች።

“ቅር የሚያሰኘኝ ነገር አለ”

ከጦርነቱ በፊት በምዕራብ ትግራይ ቃፍታ ሁመራ ነጋዴ የነበረው አፈወርቂ ገብረማርያም ሌላኛው የመጀመሪያው ተሰናባች ነው።

ከጦርነቱ በፊት ሆቴል የእርሻ ሥራ የነበረው አፈወርቂ ሠራዊቱን በ2013 የተቀላቀለው በደረሰበት መከራ እና ግፍ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ በሺህ የሚቆጠር ገንዘብም ከፍሎ በቀዬው መኖር ባለመቻሉ ወደ ሽረ መሰደዱን ገልጿል።

በነበረው የጦርነት ተሳትፎ በጥይት ተመትቶ፣ ታክሞ የዳነ ሲሆን ጦርነቱ “በጣም ፈታኝ ነበር እናም ብዙ ተምረንበታል” ይላል።

በአሁኑ ወቅት ግን ወደ መደበኛ ሕይወቱ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

“ይህን የምስጋና የምስክር ወረቀት ይዤ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ። ለትግራይ ሕዝብ ወጣሁ፣ ለትግራይ ሕዝብ ያለኝን ግዴታ ተወጣሁ፣ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፌያለሁ፣ ‘አሁን መንግሥቴ ወደ ሥዝብህ ሂድና ከሕዝብህ ጋር ኑር’ ብሎ ልኮኛል” ብሏል።

ይሁን እንጂ ሠራዊቱን ተሰናብቶ በሚሄድበት በአሁኑ የትግራይ ምዕራብ እና ደቡብ ግዛቶች እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች ከሰሜናዊ ትግራይ አለመውጣታቸው ቅሬታ እንዳሳደረበት ለቢቢሲ ተናግሯል።

“የትግራይ መሬትም ጨርሶ ነጻ አልወጣም። የተፈናቀለው የትግራይ ሕዝብ ወደ ቦታው አልተመለሰም። ሜዳ ላይ ተጥሏል፤ ወላጅ እናት እና ልጅ አልተገናኙም። በትግሉም የጠፉም አሉ” ብሏል

አክሎም “ተመልስን ለሕዝቡ ምን ብለን ነው የምንነግረው? የተሰው ጓዶቻችን ቤተሰቦች ምን ይሉናል? ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው” ሲል አጽንዖት ሰጥቷል።

በተጨማሪም ተገቢው አያያዝ እና እንክብካቤ የሚያነሱ ቢኖሩም “ ‘ይህ አልተሰጠንም፣ ይህን አልተደረገልንም’ የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አልክድም። እኔ ግን እንዲህ አልልም” በማለት ሌላ የተቀላቀለ ስሜቶች እንደፈጠረበት ተናግሯል።

ስለወደፊቱም ሲያስረዳ “መሬታችን ከዳር እስከ ዳር ነፃ እንድትሆን እንፈልጋለን፣ ሰላም እንፈልጋለን፣ ጦርነት አንፈልግም፣ ሞትም አንፈልግም” ይህ እስካልሆነ ድረስ ግን ‘ተመለሼ ወደ ሠራዊቱ ለመቀላል ዝግጁ ነኝ” ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።