የበይነ መረብ ሰርሳሪ

ከ 5 ሰአት በፊት

ለኬንያውን ወሳኝ አገልግሎት በሚሰጡ በተለያዩ ቁልፍ የመንግሥት እና የግል ተቋማት የበይነ መረብ መድረኮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኬንያ መንግሥት አረጋገጠ።

ሐሙስ ዕለት አጋጠመ በተባለው የበይነ መረብ ጥቃት የዜጎች መሠረታዊ አግልግሎት ማግኛ ተቋማት በሆኑት የሞባይል ገንዘብ ማዘዋወሪያ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ክፍያ መፈጸሚያ መድረኮች አገልግሎታቸው ተስተጓጉሏል።

በተለይም ኬንያውያን ፓስፖርት፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የነዋሪነት መታወቂያ እና የጤና አገልግሎት መረጃን ማውጣትን እና ማደስን ጨምሮ ከአምስት ሺህ በላይ መንግሥታዊ አግልግሎቶችን ለመግኘት የሚጠቀሙበት ኢ-ሲቲዝን በመባል የሚታወቀው መድረክ እክል እንደገጠመው ተገልጿል።

ጥቃቱን የፈጸሙ ወገኖች “ሥርዓቱ በተለምዶ ከሚያስተናግደው በላይ በሆኑ የአገልግሎት ጥያቄዎች እንዲጥለቀለቅ አድርገውታል። ይህም የበይነ መረብ አግልግሎቱ አዝጋሚ እንዲሆን አድርጎት ችግር ተፈጥሯል” ብለዋል የኬንያ የመረጃ፣ ኮሚዩኒኬሽን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሚኒስትር ኢሉይድ ኦዋሎ ተናግረዋል።

ነገር ግን የመረጃ መረብ ጥቃቱን የፈጸሙት “ምንም አይነት መረጃን እንዳላገኙ እና እንዳልሰረቁ” ሚኒስትሩ ለኬንያውን መረጋገጫ ሰጥተዋል።

ይህ በቁልፍ የኬንያ አገልግሎት መስጫ የበይነ መረብ መድረኮች ላይ እክልን ከፈጠረው ጥቃት ጀርባ ማን እናዳለ አስካሁን በትክክል የታወቀ ነገር የለም።

በዚህ ጥቃት ምክንያት አግልግሎታቸው የተስተጓጎለው በኬንያ የሞባይል የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ተቋማት ስም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲነሳ ቆይቷል።

ይህ በተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በይነ መረብ ላይ ያጋጠመው መስተጓጎል በርካታ ኬንያውያንን እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ነው።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበይነ መረብ በኩል ወደ አገሪቱ ለመግባት የኤሌክትሮኒክ ቪዛ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች በተፈጠረው ችግር ምክንያት እንዳይጉላሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው አሳስቧል።

ተጓዦች ኬንያ እንደደረሱ ቪዛ ሊሰጣቸው ስለሚችል አየር መንገዶች እና የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት እንዲጓዙ እንዲፈቅዱላቸው ጠይቋል።

ችግሩ የገጠማቸው መንግሥታዊ እና የግል ተቋማት ለተገልጋዮች ሁኔታውን በመግለጽ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎታቸውን መልሶ ለማስጀመር አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአገሪቱን የበይነ መረብ ደኅንነትን የሚቆጣጠረው መንግሥታዊ ተቋማም እክሉን ለማስወገድ አስፈላጊውን ሥራ እያከናወነ መሆኑን በመግለጽ፣ በተከሰተው ጥቃት ዙሪያ ምርመራ እያከናወነ መሆኑን እንዲሁም ተቋማት ስለክስተቱ ያላቸውን መረጃ እንዲያሳውቁ አዟል።