
ከ 2 ሰአት በፊት
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማራ ላ ጎ መኖሪያ ቤታቸው የሚገኙ ሠራተኞቻቸው የደኅንነት ካሜራ ምስሎችን እንዲያጠፉ ጫና አሳድረዋል የሚል ተጨማሪ ክስ ቀረበባቸው።
አዲስ በተከለሰው ክስ ዶናልድ ትራምፕ በሦስት ተጨማሪ ወንጀሎች ተከሰዋል። በዚህም በማራ ላ ጎ መኖሩያቸው ሠራተኛ የሆነው ካርሎስ ዲ ኦሊቬራም የክሱ አካል ሆኗል።
ዲ ኢሊቬራ የተከሰሰው በደኅንነት ካሜራዎች ከተያዙ ምስሎች መካከል የትኞቹ መጥፋት እንዳለባቸው በመጠየቁ መሆኑ ተገልጿል።
ዶናልልድ ትራምፕ እና ረዳታቸው ዋልት ናውታ ለቀረቡባቸው ክሶች ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ሐሙስ ዕለት ተከላክለዋል።
ናውታን እና ዲ ኢሊቬራ የፍርድ ቤቱን የምርመራ ሂደት በማስተጓጎል እንደተከሰሱ የክስ መመሥረቻ ሰነዱ ያስረዳል።
እንደ አዲሱ የክስ ሰነድ ከሆነ በተለይም የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ምስጢራዊ ሰነዶች ይቀመጡበታል ተብሎ የሚታሰበው ቦታ የሚገኙ የደኅንነት ካሜራዎች እንዲሰጡት መጠየቁን ተከትሎ ሁለቱ ግለሰቦች መረጃ ለመሰወር አሲረዋል የሚል ነው።
በክሱ እንደተብራራው ዲ ኦሊቬራ የተባለው ግለሰብ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ዳይሬክተር ሆኖ ለሚሰራ ሰው “አለቃ ሰርቨሩ እንዲጠፋ ይፈልጋሉ” የሚል መልዕክት መላኩ ተጠቅሷል።
ወዲያውኑ ዲ ኦሊቬራ ሌላኛውን ሠራተኛ በአንዲት ትንሽ ክፍል ውስጥ ካገኘው በኋላ ንግግራቸው ምስጢር ሆኖ እንዲቀር አስጠንቀቆታል። በመቀጠልም መረጃዎቹን እንዲያጠፋ አስገድዶታል ይላል አዲሱ የክስ መዝብ።
የበጋው ዋይት ሃውስ በመባል ወደሚታወቀው የዶናልድ ትራምፕ ቅንጡ ሪዞርት (ማራ ላ ጎ) ውስጥ ዲ ኦሊቬራ በማምራት የሥራ ባልደረባውን “ምን ልንሰራ እንችላለን” ብሎ መጠየቁን ክሱ አትቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ ጠበቃቸው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
- ከ50 ሺህ የሚበልጡ የትግራይ ኃይል አባላት ተሰናበቱ27 ሀምሌ 2023
- ‘ዩፎ’ እና ባዕድ ፍጡራን የተከፋፈለውን የአሜሪካ ምክር ቤት አንድ አድርገውታልከ 5 ሰአት በፊት
- የኪሊያን ምባፔ መጨረሻ የት ይሆን? ሪያል ማድሪድ ወይስ ሳዑዲ አረቢያ?ከ 5 ሰአት በፊት
አዲሱ ክስ በተጨማሪም ዶናልድ ትራምፕ ግለ ታሪክ ፀሐፊዎች ማራ ላ ጎን በጎበኙበት ወቅት ሆን ብለው ከፍተኛ ምስጢራዊ ሰነድን በቃለ መጠይቅ ላይ በመናገርም ተከሰዋል።
ይህ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ምስጢራዊ ሰነድም በአንድ አገር ላይ ጥቃት ለመፈጸም የነበረን ዕቅድ የሚያሳይ መሆኑን ክሱ አስረድቷል። ሲኤንኤን እና ሌሎች የብዙኃን መገናኛዎች እንደሚሉት ይህች አገርም ኢራን ሳትሆን አትቀርም።
“ተመልከት ምን እንዳገኘሁ… አስገራሚ አይደለም? ይህ ጉዳይ የመጣበትን ሁኔታ የሚያሳይ ብዙ ሰነዶች አሉኝ። ተመልከት” በማለት ዶናልድ ትራም ለአንደኛው ወዳጃቸው መናገራቸውን ክሱ አትቷል።
የክሱ ሰነድ በልዩ ዐቃቤ ሕግ በጃክ ስሚዝ የሚመራ ነው። ጃክ ስሚዝ ከአሁን በፊትም የ2020 ምርጫን ለመቀልበስ ትራምፕ አሲረዋል በሚለው ጉዳይ ለመነጋገር ከትራምፕ የሕግ ሰዎች ጋር ተገናኝተው ነበር።
የአሜሪካ ብዙኃን መገናኛዎች እንደዘገቡት የትራምፕ ጠበቆች ዋሽንግተን በሚኘው የጃክ ስሚዝ ቢሮ ከባለሥልጣናት ጋር ተናኝተዋል።
ትራምፕ በዚህ ጉዳይም ክስ እንደሚመሠረትባቸው ጠብቀው ነበር። ነገር ግን እስካሁን ክስ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ አዲስ የቀረቡባቸውን ክሶች ውድቅ አድርገዋል። እርሳቸውን ጥፋተኛ የሚያስብል ወንጀል እንደሌለና ከሳሾቻቸውም ይህንን ጠንቀቀው እንደሚያውቁ ዶናልድ ትራምፕ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በትራምፕ ዙሪያ የሚመሠረቱ ክሶች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። መረጃን ለመደበቅ ገንዘብ ከፍለው ሰዎችን ዝም በማሰኘት የሚቀርብባቸውን ክሶች እየጠበቁ ነው። በስም ማጥፋት ወንጀልም እንዲሁ ክስ ይጠብቃቸዋል።