
ከ 3 ሰአት በፊት
የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ደጋፊዎች፤ ከሥልጣን የተወገዱት ፕሬዝደንት ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤትን አቃጠሉ።
ደጋፊዎቹ የገዢውን ፓርቲ ጽ/ቤት ከማቃጠላቸው ባለፈ በአቅራቢያ የነበሩ መኪናዎችን ከጥቅም ውጭ አድርገዋል።
ቁጥራቸው ብዙ የማይባል መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ናቸው ወደ ፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ገብተው ጥቃት ያደረሱት።
ለመፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎቹ ድጋፍ እየሰጡ የነበሩ ሰዎች ፓርላማው አካበቢ ሠልፍ ወጥተው የሩሲያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
የጦር ሠራዊቱ ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙምን በቁጥጥር ሥር ላዋሉት ወታደሮች ድጋፉን ሰጥቷል።
ሩሲያን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ፕሬዝደንቱ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል።
አርብ ዕለት የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና፤ ፕሬዝደንቱ “በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው” ብለዋል።
ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል የተናገሩት ሚኒስትሯ መፈንቅለ መንግሥቱ “መጨረሻው” ለሆን አይገባም፤ መፈንቅለ መንግሥቱን ያቀናበሩት ሰዎች ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚሰሙ ከሆነ “መውጫ መንገድ” አለ ብለዋል።
የ64 ዓመቱ ፕሬዝደንት ባዙም ከሁለት ዓመታት በፊት ምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በምዕራብ አፍሪካ ኢስላማዊ ጂሃዲስቶችን በመታገል የምዕራባዊያን አጋር ሆነው ቆይተዋል።
- የሩሲያ እና የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለዓመታት ዝግ ወደ ነበረችው ሰሜን ኮሪያ ተጓዙ26 ሀምሌ 2023
- በሁለት ልጆቻቸው ገዳይ ላይ ስለተሰጠው የሞት ፍርድ አባት ምን ይላሉ?26 ሀምሌ 2023
- የኒጀር ወታደሮች በብሔራዊው ቴሌቪዥን መፈንቅለ መንግሥት አወጁ27 ሀምሌ 2023

መፈንቅለ መንግሥቱን ያወገዙት ዩናይትድ ስቴትስ እና የኒጀር ቅኝ ገዥ የነበረችው ፈረንሳይ፤ ዩራኒየም በተሰኘው ማዕድን በበለፀገችው አገር ወታደራዊ ካምፕ አላቸው።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን አገራቸው ለፕሬዝደንት ባዙም “የማይዛነፍ ድጋፍ” እንደምታደርግ ገልጠዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በኒጀር ያካሂድ የነበረውን ሰብዓዊ እርዳታ ማቋረጡን ይፋ አድርጓል። እርዳታው የተቋረጠው በመፈንቅለ-መንግሥቱ ምክንያት ይሁን አይሁን አልተጠቀሰም።
የመንግሥታቱ ድርጅት ከዚህ ቀደም በኒጀር 4 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ማለቱ ይታወሳል።
ሐሙስ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፕሬዝደንት ባዙም “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት እንዲለቀቁ” ጥሪ አቅርበው ነበር።
የፕሬዝደንቱ የትዊተር ገፅ ሐሙስ ጠዋት በፃፈው መልዕክት “በብዙ መከራ ያገኘናቸው ድሎች ይጠበቃሉ። ዴሞክራሲ እና ነፃነት ወዳድ ኒጀራውያን ያዩታል” ሲሉ ፅፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከምዕራባዊያን አራት ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የጦር ሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ በወታደሩ መካከል የሚፈጠር ክፍተትን ለማስወገድ በሚል መፈንቅለ-መንግሥቱን ደግፈውታል ተብሏል።
ወታደራዊው ጁንታ መሪውን ባለማሳወቁ ምክንያት በኒጀር መፈንቅለ-መንግሥቱን ማን እየመራው እንዳለ አሁንም ግልፅ አይደለም።
ብሔራዊው ቴሌቪዥን በአገር ፍቅር እና በቁርዓን ጥቅሶች መካከል መፈንቅለ-መንግሥቱ የተካሄደ ዕለት የተቀረፀውን መልዕክት ደጋግሞ በማስኬድ ላይ ይገኛል።
ነገር ግን በዋና ከተማዋ ኒያኒሚ ሱቆች ተከፍተው ሰዎች የዕለተ ከዕለት ኑሯቸውን ቀጥለዋል።
ለድጋፍ ወደ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች የሩሲያን ባንዲራ፣ “ፈረንሳይ ትውደም”፣ እንዲሁም “የውጭ ኃይሎች ይውጡ” የሚሉ መልዕክቶችን ይዘው ታይተዋል።
ፖሊስ መፈንቅለ-መንግሥቱን ደግፈው ወደ ገዢው ፓርቲ ያመሩ ሰዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።
የኒጀር ጎረቤት አገራት የሆኑት ማሊና ቡርኪና ፋሶ በተመሳሳይ በቅርብ ዓመታት መፈንቅለ-መንግሥት እንደተካሄደባቸው ይታወሳል።