
ከ 5 ሰአት በፊት
የምር እውነታው ካለ ማወቅ እፈልጋለሁ ብሏል የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ።
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ረቡዕ ዕለት ስለ ‘ዩፎ’ [ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት] ለማውራት ስብሰባ ጠርቶ ነበር።
ምስጢራዊ ስለሆኑ በራሪ አካላት የመንግሥት ከፍተኛው ምክር ቤት እንዲህ መምከሩ አዲስ ዜና ነው።
ሪብፐሊካኑ ቲም በርሼት “አረንጓዴ የለበሱ ትናንሽ ሰዎች አሊያም በራሪ አካላት አምጡልን አላልንም። እኛው እውነታውን ብቻ ነው የምንፈልገው” ይላሉ።
ሁለት ሰዓት በፈጀው ስብሰባ ሦስት እማኞች ቀርበው የፊዚክስ ሕግ ስለማይመራቸው አካላት እና ልዩ ፍጥረታት ተመልክተው ነገር ግን ስለጉዳዩ መተንፈስ ስላልተፈቀደላቸው አብራሪዎች ተናግረዋል።
ሁሉም የተስማመበት ጉዳይ እኒህ ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት፣ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ስለመሆናቸው ነው።
እርግጥ ነው እማኞቹ በጣም አስፈሪ ፍንጭ አልሰጡም፤ አሊያም ‘ኤሊየን’ (ባዕድ ፍጡራን) አሉ አላሉም። ነገር ግን ከኮንግረስ ፊት ቀርበው ጥያቄ መመለሳቸው ትልቅ ነገር ነው።
ሕግ አውጪዎች እና እማኞች ዩፎን በተመለከተ ስለሚነዙ የሤራ ትንታኔዎች ያላቸውን ጥያቄ ለጦር ሠራዊቱ አቅርበዋል።
ጡረታ የወጡት የአሜሪካ ባሕር ኃይል አዛዥ ዴቪድ ፍሬቨር፣ በፈረንጆቹ 2004 ‘ቲክ ታክ’ የሚባለውን ከረሜላ የመሰለ ቅርፅ ያለው በራሪ አካል ፊት ለፊታቸው ተገትሮ እንደነበር አውስተዋል።
ይህ ምስል በ2017 በበይነ መረብ ቢሰራጭም የአሜሪካ ባሕር ኃይል እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሰጠው ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።
“የገጠመን ቴክኖሎጂ እኛ ካለን እጅግ የላቀ፤ ምናልባትም ከ10 ዓመታት በኋላ ልናስበው የምንችለው ነው” ብለዋል።
የቀድሞው የአየር ኃይል የደኅንነት መኮንን የሆኑት ዴቪድ ግሩሽ፤ የመንግሥት ባለሥልጣናት መረጃ እንደሚደብቁ እና ምስጢር የሚያወጡ ሰዎችን ደግሞ እንደሚቀጡ ጠቁመዋል።
ይህን እንዲያብራሩ የተጠየቁት ግሩሽ በሕግ ምክንያት ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
- የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም አዳዲስ ሚሳኤሎችን ለሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር አሳዩ27 ሀምሌ 2023
- የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ለአፍሪካ አገራት ምን ጥቅም ያስገኛል?27 ሀምሌ 2023
- ሁለት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች የደም ግፊትን እንደሚቀንሱ አንድ ጥናት አመለከተ27 ሀምሌ 2023

ሰው ወይስ ሌላ?
ከደቡብ ካሮላይና የመጡት ሪፐብሊካኗ ናንሲ ሜስ እንዲህ ሲሉ ለዴቪድ ግሩሽ ጥያቄ አቀረቡ፣ ያገኛችሁት መረጃ ምን ይጠቁማል? ሰው ናቸው ወይስ ሌላ?
“ሰዎች አይደሉም። ይህ መረጃውን በተመለከተ ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ያጣሩት ጉዳይ ነው።”
ግለሰቡ ለሌላ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‘አሊየን የሚባል ነገር’ ራሳቸው በዐይናቸው አይተው እንደማያውቁ አረጋግጠዋል።
እማኞቹ የጦር ሠራዊት አባላት አሊያም ሕዝቡ ታይቶ የማይታወቅ ነገር ሲመለከቱ ሪፖርት የሚያደርጉበት መንገድ እንዲመቻች ጠይቀዋል።
ኮንግረሱ ይህን ጥያቄ ለመመለስ እጅግ ተቻኩሎ ታይቷል።
የሪፐብሊካን እና የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዮች በአብዛኛው ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ይሻል። ጥቂቶች ደግሞ ይህ ጉዳይ እውነት ነው ብሎ ማመን ተስኗቸዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት የሚዙሪው ሪፐብሊካን ኤሪክ በርሊሰን ቢሊዮን ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው የመጡ ‘ኤሊየኖች’ “ምድር ሲደርሱ ተከሰከሱ ብዬ ማሰብ አልችልም” ይላሉ።
አክለው ምናልባት እኒህ ምንነታቸው ያልታወቁ የምንላቸው በራሪዎች በወታደራዊ ተቋማት የተሠሩ አሊያም በሌሎች መንግሥታት ተሰማርተው በድብቅ ሙከራ ላይ ይሆናሉ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
በ2017 ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፤ ፔንታገን በድብቅ ዩኤፒ (unidentified aerial phenomenon) አሊያም ያልታወቁ በራሪ ክስተቶችን የሚመረምርበት ፕሮግራም አለው ማለቱ ጉዳዩ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎ ነበር።
የቀድሞው የሴኔት አብላጫ ድምፅ ሊቀ-መንበር የነበሩት ሃሪ ሪድ ‘ኤሪያ 51’ ስለተባለው ፕሮግራም ማስረገጫ ሰጥተዋል።
ኒው ዮርክ ታይምስ እና አንድ አካዳሚ በለቀቁት ምስል እኒህ ዩኤፒ የተባሉት ክስተቶች ይታያሉ።
ምንም እንኳ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የተባሉት ነገሮች ስለመኖራቸው ማረጋገጫ ቢሰጥም፣ ከየት መጡ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።