
ከ 4 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ምስጢሮችን ይዘዋል የተባሉ ኤሌክትሮኒክ መልዕክቶችን (ኢሜይሎች) ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በስህተት መላኩ ተገለጸ።
ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምስጢራዊ ኢሜሎችን እንዴት በስህተት ወደ ማሊ ሊላኩ እንደቻሉ ለማጣራት ምርመራ ጀምሯል።
ኢሜሎች መላክ የነበረበራቸው .mil የሚል ልዩ መለያ (ዶሜይን ኔም) ወደ ሚጠቀመው የአሜሪካ የጦር ሠራዊት መሆን ነበረበት።
ነገር ግን ከዚሁ የመለያ ስያሜ ላይ አንዲት ፊደል (i/አይ) በመጉደሏ ወታደራዊ መልዕክቶቹ ወደ አሜሪካ ከመሄድ ይልቅ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ የሩሲያ አጋር ማሊ ተልከዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት እንዳሉት መልዕክቶቹ የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ አልያዙም ይላሉ።
አክለው እንደሚሉት በስህተት .ml የሚል ‘ዶሜይን ኔም’ ወደምትጠቀመው ማሊ የሄዱት ኢሜሎች በቁጥር ትንሽ ናቸው።
“ቁጥራቸው ያልበዛ ኢሜይሎች በስህተት ወዳልታሰብ የኢሜይል አድራሻ እንዴት ሊላኩ እንደቻለ ለማጣራት ምርመራ ጀምረናል” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ለተሰኘው የዜና ወኪል ተናግረዋል።
“የተላኩት መልዕክቶች በጣም አስፈላጊ የሆኑ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንዳልሆኑ እርግጠኛ ነን” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለው እንደገለጹት እጅግ በጣም ምስጢራዊ የሚባሉ መረጃዎች ልውውጥ የሚደረገው መሰል ስህተትን ለመቀነስ ባለመ ሌላ መንገድ ነው።
“የመከላከይ ሚኒስቴር መልዕክት የሚላክበት መንገድ ሁሌም የሚመረመር ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መረጃ እንዴት እንደሚያዝ፣ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል እና ምስጢራዊ መረጃዎች እንዴት መቆጣጠር እንዳለብን እየመረመርን ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።
- የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም አዳዲስ ሚሳኤሎችን ለሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር አሳዩ27 ሀምሌ 2023
- የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ለአፍሪካ አገራት ምን ጥቅም ያስገኛል?27 ሀምሌ 2023
- ከ50 ሺህ የሚበልጡ የትግራይ ኃይል አባላት ተሰናበቱ27 ሀምሌ 2023
ከሳምንታት በፊት በተመሳሳይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት ኢሜይሎች በስህተት ወደ ማሊ እንደተላኩ ተዘግቦ ነበር።
ከእነዚህ ኤሚይሎች መካከል የይለፍ ቃል፣ የሕክምና መረጃ እና የከፍተኛ ባለሥልጣናት የጉዞ ደብዳቤን የመሳሰሉ ምስጢራዊ መረጃዎች ይገኙባቸዋል።
ማሊ በአህጉረ አፍሪካ ከሚገኙ የሩሲያ ጥብቅ አጋር ከሚባሉ አገራት መካከል አንዷ ናት።
ባለፈው ወር ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡት የጥቁር ባሕር የእህል ምርት ዝውውር ስምምነት ከፈረሰ በኋላ ወደ በርካታ አገራት የሚላከው ስንዴት ተቋርጧል።
ነገር ግን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ማሊን ጨምሮ ወደ ስድስት የአፍሪካ አገራት በነፃ እህል ለመላክ ቃል ገብተዋል።
የሩሲያ ባሕር ኃይል የዩክሬን ጥቁር ባሕርን የዘጋው ወረራው በተጀመረበት በየካቲት 2022 (እአአ) ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ነው።
በዚህ ምክንያት 20 ሚሊዮን ቶን የሚገመት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ አገራት መጓዝ የነበረበት እህል ባለመሄዱ የምግብ እጥረት ተፈጥሯል።
የሞስኮው ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ወታደሮች ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ ወታደሮች ጋር ተጣምረው ከጂሃዲስቶች ጋር ይዋጋሉ።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የማሊ መከላካይ ሚኒስትር፣ የአየር ኃይል እና ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከቅጥረኛው ቫግነር ቡድን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ካላቆሙ ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስጠንቅቀው ነበር።