መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ ይፋ በተደረገበት ጊዜ የእንቅስቃሴው መሪ ጄኔራል ቺያኒ በቴሌቪዥን አልቀረቡም ነበር።
የምስሉ መግለጫ,መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ ይፋ በተደረገበት ጊዜ የእንቅስቃሴው መሪ ጄኔራል ቺያኒ በቴሌቪዥን አልቀረቡም ነበር።

ከ 1 ሰአት በፊት

የፕሬዝደንቱ ክቡር ዘብ መሪ የሆኑት ጀኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ አሊያም በቅፅል ስማቸው ኦማር ቺያኒ በኒጀር የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት መሪ መሆናቸው ታውቋል።

ኒጀር ከፈረንጆቹ 1960 በኋላ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ባደረገችው ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም ከመንበራቸው ተወግደዋል።

ረቡዕ ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም. የተካሄደው መፈንቅለ-መንግሥት ኒጀርን ወደ ውጥንቅጥ የከተታት ሲሆን፣ ጎረቤቶቿ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶም ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ የመንግሥት ግልበጣ ታካሂዶባቸዋል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝደንት ባዙም የምዕራባዊያን አገራት አጋር ተደርገው ይቆጠራሉ።

ኒጀርን በቀጣናው ለሚካሄደው ፀረ-እስላማዊ ጂሃዲስት እንቅስቃሴ የአካባቢው እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ማዕከል እንድትሆን ማድረግ ችለው ነበር።

በሰሜናዊ ማሊ በ2012 የተቀሰቀሰው የአስላማዊ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ባለፉት ዓመታት ተስፋፍቶ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶን ጨምሮ የጊኒ ባሕረ-ሰላጤን አዳርሷል።

ማሊ፤ የሩሲያውን ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን መጋበዟ የፈረንሳይ ወታደሮች እና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድርጅቶች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።

አልፎም 13 ሺህ ገደማ የሚሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንቅስቃሴያቸውን እንዲገቱ ሆኗል።

ይሄኔ ነው ፕሬዝደንት ባዙም እኒህ ወደታደሮች ወደ ኒያሜይ እንዲመጡ በመጋበዝ፣ በኢስላሚክ ስቴት እና አል-ቃኢዳ ታጣቂዎች የሚቃጣውን ጥቃት ለመመከት የወሰኑት።

ፕሬዝደንቱ በገዛ ጄኔራላቸው ከሥልጣን መወገዳቸው ኒጀር ከምዕራባዊያን ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያሻክር ነው።

ኃያሉ ክብር ዘብ

በኒጀር የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት መሪ መሆናቸው የተነገረው ጄኔራል ቺያኒ የአገሪቱ የፕሬዝደንታዊ የክብር ዘብ አባል ሆነው ከ2011 (እአአ) ጀምሮ አገልግለዋል።

ኒጀር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ አራት ጊዜ መፈንቅለ-መንግሥት አስተናግዳለች። ይህን ተከትሎ ነው ከፕሬዝደንት ባዙም በፊት የነበሩት ማሐሙዱ ኢሶፉ ክብር ዘቡን ያቋቋሙት።

ሰባት መቶ ገደማ አባላት ያሉት ይህ ፕሬዝደንታዊው ክብር ዘብ “በአግባቡ ሥልጠና የወሰዱ እና የታጠቁ ወታደሮች ያሉት” ተብሎ ይገለጣል።

ምንም እንኳ ጄኔራሉ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ መፈንቅለ-መንግሥት ስለመካሄዱ ይፋ የተደረገበት መግለጫ ሲነበብ ባይታዩም የጁንታው መሪ ሆነው በቅርቡ ብቅ እንደሚሉ ተሰምቷል።

ወታደራዊ መኮንኖቹ ‘አገር ጠባቂ ብሔራዊ ምክር ቤት’ የሚል መጠሪያ የሰጡት ስብስብም መሥርቷል።

በዚህ ምክር ቤት አማካይነት ፕሬዝደንቱን ከሥልጣን ያስወገዱት “የአገሪቱ ደኅንነት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተከትሎ፤ አልፎም ምጣኔ ሃብት እና አስተዳደሩ በመበላሸቱ ነው” ብለዋል።

ኦማር ቺያኒ በ2015 (እአአ) የማሊ መሪ የነበሩት ኢሶፉን ለማውረድ በተሞከረ መፈንቅለ-መንግሥት ተሳትፈዋል ተብለው በ2018 ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲሉ አስተባብለዋል።

አንድ የግል ጋዜጣ ሐሙስ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም. ባወጣው ዘገባ ፕሬዝደንት ባዙም ከመፈንቅለ-መንግሥቱ በፊት የክብር ዘቡን መሪ ከሥልጣናቸው ሊያወርዷቸው አቅደው እንደነበር አስነብቧል።

ባለፈው ሚያዝያ ባዙም የጦር ሠራዊቱን ኤታማዦር ሹም ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናት ላይ የሹም ሽር አድርገዋል።

የፈረንሳይ ሞንድ ቲቪ5 የተሰኘው ጣቢያ ላይ ቀርበው አስተያት የሰጡ ተንታኞች፤ የኒጀር ጦር ሠራዊት በሙስና እና ዘረኝነት ያለበት ጥራት የሌላቸው መሣሪያዎች ያሉት መሆኑ የፈጠረው ቅሬታ ለመፈንቅለ-መንግሥቱ አስተዋፅዖ አድርጓል ይላሉ።

የ62 ዓመቱ ቺያኒ የጀኔራልነት ማዕረግ ያገኙት በቀድሞው ፕሬዝደንት አማካይነት በ2018 (እአአ) ነው።

ስለወታደራዊ ሕይወታቸው፣ ስለግልም ሆነ ስለትምህርታቸው ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።

በ2015 (እአአ) ከተሞከረው መፈንቅለ-መንግሥት ጋር በተያያዘ በ2018 ፍርድ ቤት በመቅረባቸው በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳ ነበር።

ራድዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል በዘገባው ጄኔራሉ መፈንቅለ-መንግሥቱን አካሂደው ፕሬዝንደንቱን በቁም እሥር ካስቀመጧቸው በኋላ ሌሎች ወታደራዊ ክንፎችን አሳምነዋል ብሏል።