July 28, 2023 – EthiopianReporter.com

ዮሐንስ አንበርብር

July 26, 2023

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ (USTR) ጽሕፈት ቤት የአጎዋ ንዑስ ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያ ለ2024 (እ.ኤ.አ.) የአጎዋ ተጠቃሚነት ብቁ መሆኗን ለመለየት ግምገማ ማካሄድ ጀመረ።

ንዑስ ኮሚቴው ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የባለድርሻ አካላት ውይይት (Public Hearing ) ማካሄዱ የታወቀ ሲሆን፣ በዚህም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የሌሎች ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮችን ብቁነት ለመገምገም ውይይት አካሂዷል።

ንዑስ ኮሚቴው ማካሄድ ከጀመረው የባለድርሻ አካላት ውይይት በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የገበያ ዕድሉ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል ወይም አይገባም የሚለውን አገር አስመልክቶ ምክንያታዊ ድጋፍ ወይም ቅሬታ በጽሑፍ እንዲልክ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ይህንንም ለሚያካሂደው ግምግማ በግብዓትነት ይጠቀምበታል።

በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነትን በተመለከተ የድጋፍና የተቃውሞ ክርክሮችን በጽሑፍ የተቀበለ ሲሆን፣ ባለፈው ሰኞ በበይነ መረብ አማካይነት ባካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይትም፣ በኢትዮጵያ ላይ ድጋፍና ቅሬታቸውን ለማሰማት የጠየቁ አካላትን አድምጧል።

በበይነ መረብ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ፣ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ታግዳ እንድትቆይ እንዲሁም እግዱ እንዲነሳላት የተከራከሩ ተቋማትና ግለሰቦች ነበሩ።

ከእነዚም መካከል በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎችን በአባልነት ያቀፈው የአሜሪካ ፋሽን ኢንዱስትሪ ማኅበር ደግሞ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት መታገዷ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ኩባንያዎችንና አጠቃላይ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣና ላይ ጉልህ ጉዳት በማስከተሉና መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎች መሻሻል በማሳየታቸው ኢትዮጵያ ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ የማኅበሩና የአባል ኩባንያዎች ፍላጎት መሆኑን አስረድቷል።

በሌላ በኩል ቮን ባተን-ሞንታግ-ዮርክ (VAN BATTEN-MONTAGUE-YORK, L.C) የተባለው መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገ የፖሊሲ አማካሪና ተሟጋች ኩባንያ፣ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት ታግዳ ልትቆይ ይገባል በማለት ተከራክሯል።
ይህ ኩባንያ በበርካታ አገሮችና ግለሰቦች ተቀጥሮ ለአሜሪካ ኮንግረንስ የቀረቡ የማዕቀብና ሌሎች የፖሊሲ ውሳኔዎች እንዳይፀድቁ ወይም እንዲፀድቁና አልያም የተላለፉ ውሳኔዎች እንዲነሱ የውትወታና የመሟገት ሥራ የሚያከናውን ሲሆን፣ ሰኞ ዕለት በተካሄደው የአጎዋ ኮሚቴ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም እንዳላቆመ በመግለጽ ኢትዮጵያ ታግዳ እንድትቆይ ጠይቋል።

የአሜሪካ አልባሳትና ጫማ ማኅበር (American Apparel & Footwear Association)፣ ሳን ማር ኮርፖሬሽን (San Mar Corporation)፣ ዘ ቻይልድ ፓላስና የአጎዋ ጥምረት የሚባሉ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ መሻሻል በማሳየቱ ዕግዱ እንዲነሳ ጠይቀዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ትግራይ አክሽን ኮሚቴ (Tigray Action Committee) ፣ ቅንጅት ለአፍሪካ አድቮኬሲ (Advocacy Network for Africa (AdNA) የተባሉ የመብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚነት ታግዶ እንዲቆይ ጠይቀዋል። የአጎዋ ኮሚቴ ኢትዮጵያና ሌሎች የሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ለአጎዋ ተጠቃሚነት ብቁ መሆናቸውን ለመለየት የጀመረው ግምግማ የቀጠለ ሲሆን፣ ኮሚቴው ግምገማውን አጠናቆ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ታውቋል።