
July 26, 2023
- ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ፈሰስ አድርጌያለሁ ብሏል
የሐሰተኛ ሰነድ ተገልጋዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መሆኑንና በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነበት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሐሰተኛ ሰነድ የመገልገል ወንጀል የተጠረጠሩ 121 ጉዳዮች ላይ የወንጀል ክስ አዘጋጅቶ ለፖሊስ ማቅረቡን፣ ከዚህም በ23 ጉዳዮች ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቱን፣ 12 ያህሉ ደግሞ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ተቋሙ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም 1,733 ሐሰተኛ ማስረጃዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በማድረጉ ሊደርስ የነበረውን ጉዳት አስቀርቻለሁ ያለው አገልግሎቱ፣ ከያዛቸው ሐሰተኛ ማስረጃዎች ውስጥ 87 በመቶ ያህሉ የማንነት ማረጋገጫ መታወቂዎች፣ እንዲሁም 11 በመቶ የሚሆኑት የጋብቻ ማስረጃዎች ናቸው ብሏል፡፡
የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓለም እሸት መሸሻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ የተጠናቀቀው ዓመት አኃዛዊ የዕቅድ አፈጻጸሙ የተሳካ ነበር፡፡ ነገር ግን የሐሰተኛ ሰነድ መበራከት ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነና ይህም የሚመነጨው በሌሎች ተቋማት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የነዋሪነት መታወቂያ፣ የጋብቻ ማስረጃ (ያገባና ያላገባ)፣ በተወሰነ ደረጃ የተሽከርካሪ ሊብሬ ከሚያጋጥሙ ሐሰተኛ ሰነዶች ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዓለም እሸት፣ ተቋሙ በቻለው መጠን ባለሙያዎቹን የሐሰተኛ ሰነድ ልየታ የሙያ ሥልጠና ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመነጋገር እንዲሰጥ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ ድርጊቱን ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሆነ አክለዋል፡፡
በተለይ ‹‹ሴክዩሪቲ ፊቸር›› የሌለው መታወቂያ በከተማዋ ውስጥ መኖሩና የዲጂታል መታወቂያ ሙሉ በሙሉ ለኅብረተሰቡ አለመዳረሱን ገልጸው፣ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው ብለዋል፡፡ ‹‹መታወቂያቸውም ሆኑ የምስክር ወረቀቶች ፎርጀሪ እንዳይሠራባቸው ተደርገው ስለማይዘጋጁ ብዙ ጊዜ ሐሰተኛ ሰነድ ለሚያመነጩ ሰዎች የተጋለጡ ናቸው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አገልግሎቱ በራሱ የሚያመነጫቸው ሰነዶች ፎቶ እንዲኖራቸው (ለአብነትም ውክልና ላይ) እንደሚያደርግ፣ በተጨማሪም የባር ኮድ በመስጠት ከሲስተም ውጪ ማንም ሰው እንዳይሠራው በቀላሉ እንዲለይ ማድረጉን ገልጾ፣ ከዚህ በተጨማሪም በኦንላይን አገልግሎት መስጠት ድርጊቱን ከመከላከል ባሻገር የተገልጋዮችን እንግልት እንደሚቀንስ አስታውቋል፡፡
የሚመለከታቸው ተቋማት ለአብነትም ተቋማት የዲጂታል መታወቂያ በመስጠት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በኦንላይን መረጃውን እንዲያገኘው ቢደረግ በቀላሉ ችግሩን መለየት እንደሚቻል፣ የመሬት አስተዳደር የሚሰጠውን ካርታ ለማንና በምን ዓይነት ቁጥር እንደሰጠ ዲጂታላይዝ አድርጎ መረጃው እንዲገኝ ቢደረግ ፎርጅድ እንዳይሠራ ዝግ ማድረግ ይቻላል ሲሉ አቶ ዓለም እሸት አስረድተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት በተፋጠነ ሁኔታ በሁሉም ቦታ እንዲሰጥ በማድረግ ቢያንስ የዜጎች መታወቂያ ዲጂታላይዝ እንዲሆንና በቀላሉ ሊገኝ እንዲችል፣ በመሀሉ የሐሰተኛ ሰነዶች እንዳይመነጩ ለመገደብ የሚያስችል አሠራር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የሥራ ክፍሎች አንዳንድ ጊዜ የሚያሳልፋቸው ከመሬትና ተያያዥ አገልግሎቶች ዕገዳ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ተፅዕኖ ደርሷል የሚል ጥያቄ ሪፖርተር ያቀረበላቸው አቶ ዓለም እሸት፣ ተቋማቸው የፌዴራል ተጠሪ መሥሪያ ቤትነቱን አስታውሰው ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤት ሽያጭና ስጦታ አገልግሎት እንዳይሰጥ ብሎ በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የቤት ሽያጭና ስጦታ እንቅስቃሴ አገልግሎቶች ቢገደቡም፣ ተቋሙ በ2015 ዓ.ም. ካገኘው ገቢ 89.1 በመቶ ድርሻ ያለው የተሽከርካሪ ሽያጭና የብድር ውል እስካሁን ባልተቋረጠ ሁኔታ መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ከ897 ሺሕ በላይ ጉዳዮችንና ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተገልጋዮችን አስተናግዶ 1.77 ቢሊዮን ብር እንደሰበሰበ፣ ገቢው ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ732 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተቋሙ አስታውቋል፡፡ የተሽከርካሪ ሽያጭና የብድር ውል ስምምነቶች ከገቢው 89.1 በመቶ ድርሻ መያዛቸውን አክሏል፡፡
በሌላ በኩል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በ2015 የበጀት ዓመት 851.5 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ፈሰስ ለማድረግ አቅዶ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ ማድረጉን አስታውቋል፡፡