
July 28, 2023 – EthiopianReporter.com

ዜና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ሕይወት ሥጋት ውስጥ መውደቁ ተገለጸ
ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ሕይወት ሥጋት ውስጥ መውደቁ ተገለጸ
ቀን: July 26, 2023
ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ሕይወት ሥጋት ውስጥ መውደቁን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሰብዓዊ የድጋፍ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት፣ ምክር ቤቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰበው፣ ማክሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል፡፡
ባለፈው ሳምንት በአፋርና በአማራ ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ መገደላቸውን የገለጹት የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ፣ በዚህም ምክንያት ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ጠቁመዋል፡፡
ምክር ቤቱ በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ላይ የደረሰውን ግድያ በፅኑ አውግዞ፣ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ለሠራተኞቹ ተገቢውን ከለላና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡
ምን ያህል ዜጎች እንደ ሞቱ፣ የሞቱበት ምክንያት፣ ጥቃት ያደረሰው አካል ማን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ የሰጡት አቶ ሔኖክ፣ ጉዳዩ ጉዳት በደረሰባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት መያዙን ገልጸው፣ ድርጅቱ ተገቢውን ማጣራት ካደረገ በኋላ ለሕዝብ እንደሚያስታውቅ ገልጸዋል፡፡
በተለይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ለሞት የሚዳረጉ ከሆኑ፣ በአገር ላይ የሚያጠላው ጥላ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አቶ ሔኖክ አስረድተዋል፡፡
ለሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች መንግሥት ከለላና ጥበቃ እንዲደረግላቸው የጠየቀው ምክር ቤቱ፣ በኢትዮጵያ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲኖሩ ችግሮች ሊባባሱ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በምሳሌነት ያነሱት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወዲህ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሞት 40 መድረሱን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ዜጎች ለከፍተኛ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ቁሳዊ ጉዳቶች እየተዳረጉ ናቸው ብለዋል፡፡
በቅርቡ በጋምቤላ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በኢንታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳ፣ ዳንጎል ወረዳና በጋምቤላ ከተማ በተከሰተው ግጭት በንፁኃን ዜጎች ላይ የደረሰው ሞትና መፈናቀል ምክር ቤቱ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
በዚህም የግጭት ዓውዱ ተለዋዋጭ በመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ፣ በመንግሥት ደግሞ ልዩ ትኩረት የሚፈልግና የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ ተደርጎ መሠራት እንዳለበት የምክር ቤቱ መግለጫ ያትታል፡፡
ምክር ቤቱ አጥፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ አንደኛው መፍትሔ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ‹‹ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ›› ከምክር ቤቱ ሐሳብ ጋር የሚቀራረብ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በጋምቤላ ክልል በተከሰተው ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጾ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉ ዜጎች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡
በግጭቱ የተሳተፉ አካላትን በተመለከተ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን መግለጫ ዋቢ አድርጎ የገለጸው ድርጅቱ፣ በአንዳንድ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎችን ጨምሮ የኑዌርና የአኝዋ ብሔረሰብ ታጣቂዎች ተሳታፊ መሆናቸውን አመልክቷል ብሏል፡፡
በግጭቱ ሕይወታቸው ያለፈ ዜጎች ብዛት መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በክልሉ መንግሥት ይፋ ያልተደረገ መሆኑን፣ አንዳንድ የመረጃ ምንጮች ከ30 በላይ ሰዎች እንደ ሞቱና 20 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ተገልጿል ሲል ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በክልሉ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ግጭት አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት የመፍትሔ አቀጣጫዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፣ ዘላቂና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ድርጅቱ አሳስቧል፡፡