July 28, 2023 

 (አዲስ ማለዳ) የኬንያው ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ ከትናንት ጀምሮ ለኹለት ቀናት በሩስያዋ ሴንት ፒተርስበርግ በሚካሄደው የሩስያ አፍሪካ መሪዎች ስብሰባ እንደማይሳተፉ ተገልጿል።

ፕሬዘዳንቱ በስብሰባው ላይ የማይገኙትም ሩስያ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር የምታደርገው ጉባኤ በአፍሪካ ኅብረት መወከል አለበት የሚል አቋም ይዘው መሆኑ ዘኢስት አፍሪካ ዘግቧል።

የፕሬዘዳንቱ ቃል አቀባይ ሁሴን መሀመድ ዊሊያም ሩቶ በሩስያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ እንደማይሳተፉ ገልጸው፤ ይህም አፍሪካ ከአጋሮቿ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ወጥ ሥርዓት ሊበጅለትና በአፍሪካ ሕብረት ሊወከል ይገባል ከሚለው አቋማቸው ጋር የተገናኘ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም፤ ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ በጉባኤው በአፍሪካ ሕብረት ልዑካን መወከላቸውን እና ኬንያ ለጉባኤው ስኬት ያላትን የመልካም ምኞች መልዕክትም በሕብረቱ ተወካዮች በኩል መላካቸውን ጠቁመዋል።

የኬንያው ፕሬዘዳንት ሩስያና አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች የበለጸጉ አገራት ከአፍሪካ መሪዎች ጋር የሚያደርጉት ስብሰባ ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ፤ ከአፍሪካ ጋር የሚደረጉ እንዲህ ዓይነት ጉባኤዎች ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ብቻ መሆን አለበት ሲሉ ይደመጣሉ።

ፕሬዘዳንቱ ይህ ዓይነቱ ድርጊት አንድም ለአፍሪካ መሪዎች ያለውን ንቀት ያሳያል የሚሉ ሲሆን፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት በለደን በተፈጸመው የንግስት ቪክቶሪያ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ የአፍሪካ መሪዎች እንደተማሪ በአውቶብስ ታጭቀው እንዲጓዙ መደረጉን አንስተዋል።

ፕሬዘዳንቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ሳይቀር ለአፍሪካ አገራት ብድር የሚሰጡበትን የተጋነነ የወለድ ምጣኔ በመጥቀስ፤ ተቋማቱ በተለይ ለድሃ አገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያረጋግጡ ዘንድ መሻሻል ማድረግ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።

በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ትናንት እና ዛሬ በሚካሄደው ኹለተኛው የሩስያ አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስር ዐብይ አህመድን እና ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

የመጀመሪያው የሩስያ አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በፈረንጆች 2019 የተካሄደ ሲሆን፤ በኮቪድ ወረርሽኝ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ትናንት የተጀመረው ኹለተኛው ጉባኤ፤ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ በተለይ ከአሜሪካና አውሮፓ ጋር ቁርሾ ውስጥ የገባችው ሩስያ፣ በአንጻሩ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የያዘችው ሰፊ እቅድ አንድ አካል ተደርጎ ይታያል።