July 28, 2023

(አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን፣ ጌራ ወረዳ ቦርጮ ዴካ ቀበሌ ግብር ከፍለው ደረሰኝ የጠየቁ አርሶ አደሮች በወረዳው የመንግሥት ሥራ አመራሮች እና የጸጥታ አካላት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አዲሰ ማለዳ በቦታው ከነበሩ የዓይን እማኞች ሰምታለች።

በቁጥር አራት የሚሆኑ አርሶ አደሮች በሕጋዊ መንገድ ግብር ከከፈሉ በኋላ ደረሰኝ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው እና ደረሰኝ ሲከለከሉ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው አካላት ሄደው ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ነው የተገለጸው፡፡

አርሶ አደሮቹ ሕጋዊ መንገድን ተከትለው አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም፤ የወረዳው የመንግሥት ሥራ አመራሮች እና የጸጥታ ኃይሎች ሐምሌ 18/2015 ላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ ስብሰባ ብለው ጠርተው አርሶ አደሮቹን እንደበደቧቸው እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙባቸው ተነግሯል።የወረዳው የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲንቃ አባኦሊ ከአራቱ አርሶ አደሮች በዕድሜ የገፉትን በሰዎች ፊት ልብሳቸውን እንዳስወለቋቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የወረዳው የብልፅግና ጽህፈት ቤት አደረጃጀት ኃላፊ አወል ጅሃድ እንዲሁ ኹለቱን ወጣት አርሶ አደሮች መሬት ላይ እንዲንበረከኩ ካዘዙ በኋላ አልንበረከክም ያለው ወጣት ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን ነው በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞቹ የተናገሩት።

አርሶ አደሮች በእስር ላይ እንደሚገኙ በመግልጽ፣ ይህንን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እና የታሰሩት አርሶ አደሮችም እንዲፈቱ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የጌራን ወረዳ አስተዳዳሪ ሐዊ ሰዒድን ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠናል፣ በዚህም እጅግ እናዝናለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናረግረዋል፡፡

አክለውም ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት የወረዳችንን እንዲሁም የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉ እና ስነምግባር የጎደላቸው ናቸው ካሉ በኋላ፤ ወንጀሉን በፈጸሙ የወረዳው የመንግሥት ሥራ አመራሮች ላይም ሆነ የጸጥታ አካላት ላይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።